አካታች ብሔራዊ ምክክሩን ከማሳካት አንፃር የምሁራንን ሚና የሚዳስስ የምክክር መድረክ  እየተካሄደ ነው

የካቲት 5/2014 (ዋልታ) “አካታች ብሔራዊ ምክክሩን ከማሳካት አንፃር የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ የሠላም ሚኒስቴር ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለምን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታ ታየ ደንደአ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን እና ስትራቴጅ ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ዘውዱ እምሩን (ዶ/ር) እና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እየተሳተፉ መሆኑ ተገልጿል።

እንደ ሀገር በሠለጠነ መንገድ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ መሻገርን መለማመድ እና ለትውልድም ማሻገር ይገባል ያሉት የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም የዜጎች ደኅንነት የተረጋገጠበት፣ ሠላም የሠፈነበት እና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲመሠረት የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ይገባል ብለዋል፡፡

ለትውልዱ አዲስ ምዕረፍ መክፈት ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ ከጥላቻ ፍረጃና የተዛቡ ትርክቶች ወጥተን በሠለጠነ መንገድ መወያየት፣ ሀሳብና ልዩነትን ማክበር የሚቻልበት ሀገር እንዲሆን የተግባር ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ ምሁራን ለዚህ ስኬት ሚናቸው የጎላ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን እና ስትራቴጅ ኮሚዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ዘውዱ እምሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ችግሮችን በአመክንዮና ውጤት የሚመሩ ምሁራን የሚገኝባቸው እና የሚፈራባቸው በመሆኑ በሠላም ግንባታ እና እንደሀገር የተወጠነው ምክክር ውጤታማ እንዲሆን ከዚህ ተቋም ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።

ምክክሩን ገለልተኛ የሕዝብ ምርጫ የሆኑ ግለሠቦች የሚመሩት እንደሆነና መንግሥት፣ ምሁራን፣ ሲቪክ ማኅበራት እና መላ ኅብረተሰቡ የጋር ርብርብ በማድረግ ይህን አዲስ ምዕራፍ ስኬታማነት በቅንነት ለውጤት ሊሠሩ እንደሚገባም መገለጹን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡