አክሱም ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን ጥር 20 እና 21 ተቀብሎ እንደሚያስተምር አስታወቀ

 

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን ጥር 20 እና 21 በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ኹሓ ካምፓስ ተቀብሎ እንደሚያስተምር አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብረእየሱስ ብርሃነ የመማር ማስተማር ሂደትን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

“በትግራይ ክልል እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ተቋርጦ የነበረው የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ኹሓ ካምፓስ ይጀመራል” ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተደረገ ውይይት ተመራቂ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ተማሪዎችም ሆኑ ወላጆች የደህንነት ስጋት ሳይገባቸው በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ተመራቂዎቹ መገኘት እንዳለባቸው በመግለጽ ጥሪ አቅርበዋል።

በቀጣይም ሌሎች ተመራቂ ላልሆኑ ተማሪዎች ጥሪ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው የሚያስተምር መሆኑንም ገልጸዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና የመሰረተ ልማት ጉዳዮች ዳይሬክተር ሰለሞን አብርሃም፣ መንግስት በትግራይ ክልል ባካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሂደት ተስተጓጉሎ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዋናነት በአክሱም እና በአዲግራት ዩኒቨርሰቲ የመማር ማስተማር ሂደቱን ማስቀጠል እንዳልተቻለም አንስተዋል።

የመቀሌ እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ማስመረቃቸውን አስታውሰው፣ በአክሱም እና አዲግራት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ እንዲቀጥል የማመቻቸት ስራ መስራቱን ገልፀዋል።