አዋጭ 15ኛ የምስረታ በዓሉን እያከበረ ነው

ሰኔ 12/2014 (ዋልታ) አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበር 15ኛ የምስረታ በዓሉን “አዋጭ በአዋጭነት ለ15 አመታት“ በሚል መሪ ቃል እያከበረ ነው፡፡
ማኅበሩ ለማኅበረሰቡ የቁጠባ ባህል እንዲዳብር እና የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል አንግቦ በ33 ሴት እና በ8 ወንድ በድምሩ በ41 መስራች አባላት በ15 ሺሕ 237 መነሻ ብር መመስረቱን የማኅበሩ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዘሪሁን ሸለመ ተናግረዋል፡፡
ማኅበሩ አሁን ላይ የአባላት ቁጥሩን 75 ሺሕ በማድረስ የካፒታል አቅሙንም በማስፋፋት ለበርካታ ዜጎች የቁጠባ ባህል እንዲዳብር በማድረግ 15 ዓመት በተሳካ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አክለው የገለፁት::
ማኅበሩ ባለፉት 15 አመታት አስቸጋሪ የሆኑ ጉዞዎችን በፅናት በማለፍ እና መቆጠብ የስልጣኔ መንገድ መሆኑን አላማው አድርጎ በመንቀሳቀስ አሁን ላለበት ደረጃ ሊደርስ መቻሉም ተገልጿል፡፡
በመድረኩ በርካታ የማኅበሩ አባላትን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ፡፡
በአመለወርቅ መኳንንት