አየር መንገዱ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የመንገደኞች አውሮፕላን ወደ ጭነት የመቀየር ስራ አጠናቀቀ

ጥቅምት 3/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ቢ767 የመንገደኞች አውሮፕላን ወደ ጭነት ማጓጓዣነት ቀይሮ አጠናቅቋል።

አየር መንገዱ ከእስራኤል ኤሮስፔስ ኢንዱስትሪ ጋር በመተባበር ነው ከሶስት ቢ767 የመገደኛ አውሮፕላኖች ውስጥ አንዱን ነው ወደ ጭነት ማጓጓዣነት ቀይሮ ያጠናቀቀው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ቅያሬው በእድሜ የገፉትን አውሮፕላኖች ወደ ጭነት በመቀየር የጭነት አቅምን ለማሳደግና በምትካቸው ለመንገደኞች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቁ እና ምቹ አውሮፕላኖችን ለመተካት ታስቦ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

የጭነት እና የጥገና አቅምን በማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን አየር መንገዱ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒ ኤች ዲ) የአውሮፕላን ቅያሬው የቴክኖሎጂ እና እውቀት ሽግግር ከማድረግ በዘለለ ኢትዮጵያን የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑን ተናግረዋል።

አየር መንገዱ ሁለተኛውን የመንገደኞች አውሮፕላን ወደ ጭነት የመቀየር ስራውን በቅርቡም እንደሚያጠናቅቅ ተገልጿል።

ይህ በአየር መንገዱ የስኬት ታሪክ ሌላ ተጨማሪ የመሰረት ድንጋይ የሚጥል እና ከመንገደኛ ማጓጓዣ ባለፈ በጭነት አገልግሎትም የአፍሪካ መሪ አየርመንገድ ለመሆን የወሰደው ታላቅ እርምጃ ነው መባሉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።