አየር መንገዱ የአቪየሽን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ተባለ

ጥቅምት 15/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዘመኑን የአቪየሽን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱንና የአፍሪካ ኩራትነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሊቀ-መንበር ግርማ ዋቄ ገለጹ።

አየር መንገዱ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ኢኮኖሚው ውስጥ የላቀ ሚናውን እየተወጣ እንደሆነም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሰባ ዓመታት በላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አንግቦ በመብረር የሀገር መለያ አርማና የአፍሪካ ኩራት ለመሆን በቅቷል።

የአየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሊቀ-መንበር ግርማ ዋቄ እንደገለጹት አየር መንገዱ በየአምስት ዓመቱ በእጥፍ የማደግ እቅዱን በስኬት እየተገበረ ይገኛል ብለዋል።

ተቋሙ በዓለም የአቪየሽን ዘርፍ የዘመኑን ምርጥ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀምና አዳዲስ አውሮፕላኖችን ቀድሞ በማስገባት እንደሚታወቅ ጠቁመው፤ ይህን በማስቀጠል የቀዳሚነት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በዚህም በዓለም ላይ ያለውን ብቁ ተወዳዳሪነትና የአፍሪካ ኩራትነቱን አስጠበቆ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አየር መንገዱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ከማዋል ባሻገር በዘርፉ ብቁ ቴክኖሎጂን መሠረት አድርገው የሚሠሩ ባለሙያዎችን ማፍራቱን በትኩረት እየሠራበት ነው ያሉት።

በተለይም ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የዘመኑን ቴክኖሎጂዎች በራስ አቅም የመጠገንና በምልስ ምህንድስና ለተፈለገው ዓላማ ለመጠቀም የሰው ኃይል በማሰልጠን ወደ ሥራ እንደሚያሰማራም ገልጸዋል።

 

አየር መንገዱ ዓለም ዓቀፍ መዳረሻዎቹንና ገበያውን በማስፋት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

 

በተለይ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ አየር መንገዱ የላቀ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2021 ከ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያገኘ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከ130 በላይ ዓለም አቀፍና 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች ያሉት መሆኑ ይታወቃል።