አደንዛዥ ዕፅ በማዘዋወርና በመጠቀም የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አደንዛዥ ዕፅ

መስከረም 25/2014 (ዋልታ) በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የጭሮ ከተማ ፖሊስ አደንዛዥ ዕፅ ሲጠቀሙና ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎችን ዛሬ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

የጭሮ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሚካኤል ዳኜ እንደገለጹት ግለሰቦቹ አደንዛዥ ዕፁን ከሚያመርት ሰው በመረከብ ለሌሎች በማከፋፈል እንዲሁም ከሸቀጦች ጋር ሲሸጡ ተደርሶባቸዋል።

ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በተጠርጣሪዎች ቤት ባደረገው ፍተሻ 20 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ ዕፅ እንደተገኘባቸው አስረድተዋል፡፡

በግቢው ውስጥ ሀሺሽ ዘርቶ እያስፋፋ ያለ ግለሰብ ለጊዜው ሸሽቶ ቢያመልጥም በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝም ኢንስፔክተር ሚካኤል አስታውቀዋል፡፡

አደንዛዥ ዕፅ ሲጠቀምና ሲያዘዋውር በቁጥጥር ስር የዋለው አንዱ ግለሰብ በሰጠው አስተያየት፤  ቀደም ሲል በድለላ ስራ ይተዳደር እንደነበርና ከጓደኞቹ ጋር በአጋጣሚ እንደመዝናኛ እንደጀመረው ተናግሯል።

አደንዛዥ ዕፁን የሚያገኘው በምዕራብ ሐረርጌ መጣቀሻ ጢቆ ከምትባል አካባቢ የሚኖር ግለሰብ ከሌሎች የሰብል ምርቶች ጋር ቀላቅሎ እያመረተ እንደሚያመጣለት አስረድቷል፡፡

ሌላዋ ተጠርጣሪ በበኩሏ፣ ማንነቷን የማታውቃት ሴት ከአዲስ አበባ እያመጣች እንዴት እንደሚሰራ ስልጠና ከሰጠቻት በኋላ ወደ ስራው እንዳስገባቻት ተናገራለች፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ከልጆቿና ሌሎች ሰዎች ጋር የነበራትን መልካም ግንኙነት በመበላሸቱ መረበሿንና በዚህም መፀፀቷን እንደገለጸች ኢዜአ ዘግቧል።