አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የተቀረጸ መሆኑ ተጠቆመ

ጥር 22/2014 (ዋልታ) አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በቀጣዮቹ ዓመታት በሀገሪቱ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንዲያስችል ተደርጎ በሰፊ ጥናት የተቀረጸ መሆኑን የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የነባሩን ሥርዓተ ትምህርት ችግሮችና ክፍተቶች በጥናት በመለየት በልዩ ትኩረት የተዘጋጀ መሆኑም ተጠቁሟል።
ቢሮው በወላይታ ሶዶ፣ ሆሳዕናና ዲላ ማዕከላት ለሙከራ ትግበራ ለተመረጡ 100 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን የመማሪያ ማስተማሪያ መጽሐፍት 2ኛ ዙር የትውውቅ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና የመምህራንና ትምህርት አመራር ልማት ዘርፍ ኃላፊ ዳዊት ፋንታዬ እንዳሉት አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የዘርፉ አካላትን ተጠያቂነት የሚያሰፍን የህግ ሥርዓት እንዲኖረው ተደርጓል።
ትምህርት ሁሉንም የሀገራችን ችግሮችና ጉድለቶች የሚቀርፍ በመሆኑ ተገቢነቱ፣ ጥራቱ፣ ችግሮቹና ጉድለቶቹ ላይ ሕዝቡን ያሳተፈ ጥናትና ምርምር መደረጉንም ተናግረዋል።
በሁለተኛው ዙር የትውውቅ ስልጠና ከ1 ሺሕ 200 በላይ መምህራን ተሳታፊ እንደሆኑ የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡