አዲስ አበባ ያስተናገደቻቸው ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በሰላም መጠናቀቃቸውን የጋራ ግብረ ኃይሉ አስታወቀ

መጋቢት 5/2014 (ዋልታ) አዲስ አበባ ያስተናገደቻቸው ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በሰላም መጠናቀቃቸውን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

ዝግጅቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ ትብብር ላደረጉ አካለት እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለተወጡ መላው የፀጥታ አካላት ግብረ ኃይሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በአዲስ አበባ ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም አንደኛውን የብልፅግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤውን እንዲሁም መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የአስከሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት በመስቀል አደባባይ እንዲሁም መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም በመንበረ ፀበኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን የፀሎት፣ የሽኝትና የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው መፈጸሙን አመልክቷል፡፡

በተመሳሳይ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም ታለቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለ19ኛ ጊዜ ያዘጋጀው የ5 ኪሎ ሜትር የሴቶች ሩጫ በሰላም መካሄዱን ጠቁሟል፡፡