አዲስ ዋልታ ለፊላ ሙዚቃ የሰጠው እውቅና ፊላን ለዓለም ለማስተዋወቅ የምናደርገውን ጥረት ያግዛል – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ግንቦት 28/2016 (አዲስ ዋልታ) አዲስ ዋልታ ለፊላ ሙዚቃ የሰጠው እውቅና ፊላን ለዓለም ለማስተዋወቅ የምናደርገውን ጥረት ያግዛል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት በደሞ አዲስ የሙዚቃ ተሰጥኦ ውድድር ማጠቃለያ ላይ ለፊላ ሙዚቃ የእውቅና ሰርተፍኬት መስጠቱን ተከትሎ ለአዲስ ዋልታ በላኩት መልዕክት የክልሉ መንግስት የፊላ ሙዚቃ በዩኔስኮ እውቅና እንዲሰጥ እየሰራ ላለው ስራ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸው ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለአዲስ ዋልታ የላኩት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

በዲራሼዎች ዘንድ አጅግ ተወዳጅ የሆነው የፊላ ሙዚቃ ሶስት መሠረታዊ ትርጓሜዎች አሉት፡፡ በአጭሩ ፊላ ሶስት ነገሮችን ይወክላል፡፡ ፊላ ሙዚቃ ነው፣ ፊላ ዳንስ ወይም ውዝዋዜ ነው እንዲሁም ፊላ የሙዚቃ መሳሪያ ነው፡፡ መሳሪያዎቹና ተጫዋቾቹ ብዛታቸው ዝቅተኛው 24 ሆኖ ስምንት ስምንት በመጨመር እስከ 48 የሚደርሱበት ጊዜ አለ፡፡

ይህንን ድንቅ የሆነውን የፊላ ጨዋታ ሙዚቃና ውዝዋዜ ለዓለም ለማስተዋወቅ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ከቅርስ ጥበቃ ባስልጣን፣ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና ከጋርዱላ ዞን ጋር በመሆን በዓለም በተባበሩት መንግሥት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) በማይዳሰሱ የሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት ለማስመዝገብ የጥናት ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

በዲራሼዎች የአዝመራ ወቅት ከነሐሴ ወር ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ የሚዘልቀው መኸር ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የሚገኘው ምርት በአንጻሩ ከበልግ ያነሰ ቢሆንም የዓመቱ ማጠቃለያ በመሆኑና የአዲስ ዓመት ዋዜማ በመሆኑ ደስታው ከፍተኛ ነው፡፡ ታኅሣሥ ምርት የሚሰበሰብበት ሲሆን ጥር የጋብቻ፣ የድግስ፣ የፈንጠዝያና የጭፈራ ወር ነው፡፡


የዲራሼ ካላዎች (working groups) ለዓመታት ያጠራቀሙትን ገንዘብ አውጥተው ሠንጋ እየገዙ መንደሮችን ሁሉ ድግስ በድግስ የሚያደርጉበት ወር ነው ወርሃ ጥር፡፡ በየመንደሩ ፊላ የሚሰማበት የፈንጠዝያ ወር ነው፡፡ በማህበር የሚበሉበት ኮራ ጅንን ብለው የደስታ ሽሎታ የሚጫወቱበት ወር ነው ወርሃ ጥር፡፡ ይህ ታላቅ ወር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጆች ሁሉ ቅርስ ይሁንልኝ ብላ ካስመዘገበችው ታላቁ የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ወር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ነው የክርስትና ሐይማኖት እና የዲራሼዎች ሐይሶት (ዕረፍት) በዓል የተገናኙት፡፡

በዚህ ምክንያት ፊላ የባህል ጨዋታ ብቻ ሳይሆን የሐይማኖቱ ተከታይ ዲራሼዎች ታቦታትን በታላቅ አክብሮት በፊላ አጅበው ከሸኙ በኃላ ወደየ አደባባዮቻቸው (ሞራ) ተመልሰው በባህላዊ ጨዋታዎች መንደሮቻቸውን ያደምቁበታል፡፡

የጥምቀት በዓል በዲራሼ ምድር ለየት ባለ መልኩ ይከበራል፡፡ በአብዛኛው የኢትዮጵያ አከባቢ ጥምቀት የአደባባይ በዓል ሲሆን ዲራሼ ግን በወርሀ ጥር ዘመን ይቀይራል “ሀይሶት ህርባ” ብሎ፡፡

ፊላን ለዓለም ያስተዋወቁት የኢትዮ-ጃዝ አባት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ ናቸው፡፡ ፊላ የተለየ እና ዓለም ያላትን የሙዚቃ የሳይንስ ግኝት ሊቀይር የሚችል ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ፊላ የበለጠ እየተቀናበረ ከጃዝ ሙዚቃ የመናበብ ዕድል አለው ሲሉም ይደመጣሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፊላ በሀገሪቱ በሚከናወኑ ሙዚቃ፣ ባህል እና ኪነጥበብ ነክ ዝግጅቶችና መድረኮች ላይ እጅግ ተመራጭና እውቅና የሚሰጠው ፕሮግራም ሆኖ ይስተዋላል። በርካታ የግልና የመንግስት የዘርፉ አጥኚዎች ጥናት ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩና እያጠኑም ይገኛሉ፡፡

ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ደሞ አዲስ በተሰኘው የሙዚቃ ተሰጥኦ ውድድር ማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ለፊላ ሙዚቃ የእውቅና ሰርተፍከት ሰጥቷል። የተሰጠው እውቅና የክልሉ መንግስት የፊላ ሙዚቃ ለማስተዋወቅ እና በዓለም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት እውቅና እንዲሰጥ እየሰራ ላለው ስራ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነውና ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።