አዲስ የሲሚንቶ ዋጋ ተመን ይፋ ሆነ

ገብረመስቀል ጫላ

መስከረም 4/2015 (ዋልታ) እየጨመረ የመጣውን የሲሚንቶ ምርት ዋጋ ለማስተካከል አዲስ የዋጋ ተመን ማውጣቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ እየናረ የመጣውን የሲሚንቶ ምርት ዋጋ ለማስተካከል ፋብሪካዎች የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ተጠይቀው ያወጡት ዋጋ እጅግ የተጋነነ በመሆኑ ነው በዘርፉ ያለውን የምርት ሂደት ጥናት የሚያደርግ ቡድን በማቋቋም አዲስ የዋጋ ተመን ይፋ ያደረገው፡፡

በዚህ መሰረት ሲሚንቶ ከፋብሪካ የሚወጣበት አዲሱ የዋጋ ተመን ዝቅተኛው 510 ብር ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 683 ብር ከ44 ሳንቲም እንዲሆን ተወስኗል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ አሁን ላይ የሲሚንቶ ምርት እጥረት በመኖሩ ለመንግስታዊ ስራዎች ቅድሚያ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችም ከሚመለከተው የመንግስት ተቋም ማረጋገጫ በማምጣት ከፋብሪካዎች በቀጥታ ምርት የሚገዙበት መንገድ ተመቻችቷል ብለዋል፡፡

የግል ተጠቃሚዎችን በተመለከተም የሁሉም ከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች ፍላጎት ምን ያህል እንደሆነ ስለሚታወቅ በመንግስት የልማት ድርጅቶችና በተደራጁ ማህበራት በኩል እንደሚያገኙ አስረድተዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች ይሁንታ ካገኙ አካላት ውጪ ሲሚንቶ ይዞ የሚገኝና በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ግብይቶች ህገወጥ በመሆናቸው ተቋሙ ማስታወቂያ ካስነገረበት ቀን ጀምሮ ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

በከተሞች ላይ የሚኖረው ሽያጭም የትራንስፖርት፣ የጫኝና አውራጅ እንዲሁም የመጋዘን ኪራይን ታሳቢ በማድረግ የሚሸጥ ይሆናል መባሉን የኤፍቢሲ ዘገባ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW