አገልግሎቱ አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት እና ጥቅም እንዲረጋገጥ ሁሉም ተባብሮ እና ተደማምጦ የሚሰራበት እንዲሆን ምኞቱን ገለጸ

ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ

መስከረም 1/2015 (ዋልታ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት እና ጥቅም እንዲረጋገጥ ሁሉም ተባብሮ እና ተደማምጦ የሚሰራበት እንዲሆን ምኞቱን ገለጸ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ ለመላው ኢትዮጵያዊያን የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም መጪው አዲስ ዘመን ለኢትዮጵያውያን ሰላም፣ መቻቻል፣ መከባበርና መፈቃቀድ የሰፈነበት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት እና ጥቅም እንዲረጋገጥም ሁሉም ተባብሮ እና ተደማምጦ የሚሰራበት እንዲሆን ምኞቱን ገልጸዋል።

‹‹መላው ኢትዮጵያዊያን እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ። አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤናና የስኬት እንዲሆን በራሴ እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመራሮች እና ሠራተኞች ስም መግለጽ እወዳለሁ›› ያሉት አቶ ተመስገን በተለይ የኢትዮጵያን ህልውና ለማረጋገጥ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በግዳጅ ላይ የምትገኙ የጀግናው የመከላከያ ሠራዊት እና የጥምር ጦሩ አባላት መላው ሕዝብ የሰላም አየር እንዲተነፍስ የሕይወት ዋጋ ጭምር እየከፈላችሁ በመሆኑ ክብር ይገባችኋል ብለዋል፡፡

‹‹ውድ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አዲሱ ዓመት ለሰላም በምትከፍሉት መስዋዕትነት በአዳዲስ የድል ብሥራቶች የሚታጀብ እንደሚሆን በልበ ሙሉነት እገልጻለሁ፡፡ እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ›› ያሉት አቶ ተመስገን፤ የተቋሙ አባላትም የሥጋት ቀጣና በሆኑ አውደውጊያዎች ጭምር በመሠማራት መረጃ በመሰብሰብ፣በመተንተንና ለሚፈለገው አላማ እንዲውል በማድረግ ሀገራዊ ግዳጃቸውን እየተወጡ በመሆኑ አክብሮቴና የአዲሱ ዘመን መልካም ምኞቴ በያሉበት ይድረሳቸው ብለዋል፡፡

በመልዕክታቸው ኢትዮጵያ ሰላምን አበክራ ትሻለች፡፡ የሰላሙ መንገድ ዛሬም ክፍት ነው፡፡ ይህን ባለመቀበል ጦርነትን የቀሰቀሱ አካላት ዛሬም የሰላምን ዋጋ ተረድተው በአዲስ ዓመት በአዲስ መንገድ እንዲጓዙ ኢትዮጵያ ጥሪ ታቀርባለች ያሉት አቶ ተመስገን፤ በሀገር ህልውና የተቃጣውን ጥቃት ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትና የጥምር ጦሩ በብቃት መመከታቸውን ወደፊትም ይህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትም በተጠናቀቀው ዓመት ባከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች ዘመኑን የሚዋጁ ቴክኖሎጂዎች በመታጠቁና የላቀ ብቃት ያለው የሰው ኃይል አቅም በመገንባቱ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በአሸናፊነትና በጽናት እንድትሻገር ብርቱ ጉልበት ሆኗል፤ በእርግጥም ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ብለዋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!