አገልግሎቱ ወቅታዊ የደኅንነት ሥጋቶችን የሚመክቱና ቀጣይ አደጋዎችን የሚያስቀሩ የተልዕኮ ክለሳዎች ማካሄዱን ገለጸ

ነሐሴ 23/2014 (ዋልታ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በ2014 የበጀት ዓመት በሀገር ላይ ያጋጠሙን ወቅታዊ የደኅንነት ሥጋቶችን በሚገባ የመከቱና ቀጣይ አደጋዎችን ማስቀረት የሚችሉ የተልዕኮ ክለሳዎችን መሠረት ያደረጉ ስምሪቶች ማካሄዱን አስታወቋል።

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በህግ ማስከበሩ ሂደት፣ በህልውና ዘመቻው እና በ2014 ዓ.ም ዕቅድ አፈፃፀም የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ከተቋሙ ጋር በቅንጀትና በመተጋገዝ ለሰሩ ለፌደራልና ለክልል የፀጥታ አካላት እና ለሌሎች ባለድርሻዎች እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል፡፡

ተቋሙ በሸራተን አዲስ ባካሄደው የምስጋናና እውቅና መድረክ ላይ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የተለያዩ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የመረጃ ተቋማት አመራሮች፣የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ አመራሮችና አባላት እንዲሁም የተለያዩ የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት የምስጋናና እውቅና መድረኩ ዓላማ ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ላስመዘገባቸው ስኬቶች አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት እውቅናና ሽልማት በመስጠት ጠንካራ ተሞክሮዎችን በማስፋት ለቀጣይ ሃገራዊ ተልዕኮዎች ተነሳሽነት ለማጎልበት እንዲሁም ከፌደራልና ከክልል የፀጥታ አካላትና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር የተጀመረውን መተጋገዝ፣ አንድነትና ግንኙነት ማጠናከር ነው፡፡

አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በ2014 ዓ.ም የሥራ ዘመን የተቋሙ ተልዕኮዎች ላይ ክለሳ በማድረግ በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣በመረጃ ስምሪት፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በአጋርነትና ትብብር ሥራዎች ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

ተቋሙ ወቅታዊና ቀጣይ የደኀንነት ሥጋቶችን መሠረት ያደረጉ የተልዕኮ ክለሳዎች በፍጥነት በማካሄዱና ወሳኝ የሆኑ የአቅም ግንባታ መስኮችን በመለየት ወደ ተግባር መሸጋገሩ ለውጤቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አቶ ተመስገን አመልክተዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኀን ነት አገልግሎት አመራሮችና አባላት በ2014 ዓ.ም መባቻ በተካሄደው የህልውና ዘመቻ በላቀ ሀገራዊ ስሜትና ተቋማዊ እሴቶችን በመላበስ ጭምር አኩሪ ታሪክ መፈጸማቸውን ያስታወሱት አቶ ተመስገን፤እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ተጋድሎ ለፈጸሙት ጀግኖች እውቅናና ሽልማት መበርከቱ ለቀጣይ ስምሪት ጉልበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከሕዝብ፣ ከሀገር ውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን የትብብርና የአጋርነት ሥራ ይበልጥ በማጠናከር በኩል ያለፈው በጀት ዓመት ስኬታማ እንደነበር የተናገሩት አቶ ተመስገን፤ ተቋሙ የሚያካሄደውን የሪፎርም ተግባራትና የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ ለኅብረተሰቡና ለውጭ ባለድርሻ አካላት በማስገንዘብ በኩል ለመጀመሪያ ጊዜ ክፍት የተደረገው ዲጂታል ኢግዜቢሽን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

በዜጎች ዘንድ ከፍተኛ መተማመን የፈጠረው እና የተቋሙን ገጽታ በመገንባት ጉልህ ድርሻ ያበረከተው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዲጂታል ኤግዜቢሽንም የውጭ ባለድርሻ አካላት ከአገልግሎቱ ጋር በአጋርነት ትብብር የመሥራት ፍላጎታቸውን በማሳደግ ከተቋማዊ ግብ ባለፈ ሀገራዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ከፍ በማድረግ ታላቅ ስኬት ያስመዘገበ እንደነበር አቶ ተመስገን ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ ጥሪ ተደረገላቸው ከተገኙት የክልል ርዕሳን መስተዳድሮች መካከል የሶማሌ ክልላዊ

መንግስት ርዕሳን መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ በበኩላቸው የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት የመረጃ ስምሪትና ተሳትፎ አሁን እየተካሄደ ያለውን ፀረ አልሸባብ ዘመቻ ውጤታማ ማድረጉን ጠቁመው፤ ከአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የተማርነው ነገር ቢኖር ሁሉም በትብብርና በአንድንት መንፈስ ከሠራ የላቀ ውጤት እንደሚመዘገብ ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ በተጠናቀቀው 2014 የሥራ ዘመን የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት በአዲስ ምዕራፍ ላይ የተራመደበት፣ ለአዳዲስ ተልዕኮዎች ራሱን ያበቃበት፣ መጪውን ዘመን የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ራሱን ያዘጋጀበት፣ ከፊቱ ያሉትን ዕድሎችና ሥጋቶች በሚመጥን መልኩ ለነገ እራሱን ዝግጁ ያደረገበት እንደሆነ የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ ገልጿል፡