አገራዊ ምክክሩ ሕገመንግሥታዊ ጉዳዮችን ለማሻሻል ይረዳል ተባለ

ታኅሣሥ 22/2014 (ዋልታ) አገራዊ ምክክሩ እንደ ሕዝብ ሳንወያይባቸው የፀደቁ የተለያዩ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን ለማሻሻል ይረዳል ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ ተናገሩ።
ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት በኢትዮጵያ አካታች አገራዊ ምክክር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል። በምክክሩ ስለ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ይነሳል ተብሎ ይጠበቃል፤ በዚህም ሕዝብ ሳይስማማባቸው የፀደቁ የሕገ መንግሥት አንቀጾችን ለማሻሻል የሚረዱ የመነሻ ሐሳቦችን ማግኘት ይቻላል ብለዋል።
አሁን ያለው ሕገ መንግሥት የሕዝብ ይሁንታን አግኝቶ የወጣ አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ተስፋዬ፣ ‹ሕገመንግሥቱ ላይ የተወያዩት የትሕነግ የፖለቲካ ካድሬዎች ናቸው፤ ለካድሬዎቹ ደግሞ ይሁንታን አልሰጠናቸውም› የሚሉ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ለኢፕድ ገልጸዋል።
ሁሉን ዐቀፍ አገራዊ ምክክር ያስፈልጋል መባሉ የሕዝብን ፍላጎት ይበልጥ ለማስተናገድ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ አገራዊ መድረክ መዘጋጀቱ ሕጉ ሲወጣ አልተሳተፍንም ለሚለው ሰፊው ሕዝብ ሃሳቡን እንዲሰጥ ዕድል የሚፈጥር ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅብረተሰቡ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዕጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ የሚሰጥባቸውን አማራጮች ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት፦
የአማርኛ ፌስቡክ ገፃችንን ይወዳጁ ይከተሉ
ከአረብኛ ፌስቡክ ገፃችን ጋርም ይጓዙ
የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
የትዊተር ገፃችንን ይከተሉ
አብራችሁን ስለሆናችሁ ደስተኞች ነን!