አገራዊ የምክክር መድረኮች በቀጣይ ዓመት ኅዳር ወር ይጀመራሉ ተባለ

ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

ግንቦት 6/2014 (ዋልታ) አገራዊ የምክክር መድረኮች በቀጣይ ዓመት ኅዳር ወር እንደሚጀመሩ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

አገራዊ ምክክሩ የቅድመ-ዝግጅት፣ ዝግጅት፣ ምክክር እንዲሁም የትግበራና ክትትል የተሰኙ አራት ምዕራፎች መኖራቸውን የገለጹት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ እስካሁን ባለው ሂደት የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች መካከል ዋነኛ የሆነው የእቅድ ሥራ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ተጠናቆ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ግምገማ እንደሚደረግበት ገልጸዋል።

በተያዘው ክረምት ደግሞ የዝግጅት ምዕራፎች ተጠናቀው በመጭው ዓመት ኅዳር ወር ላይ የምክክር መድረኮች እንደሚጀመሩ ነው የገለጹት።

የዝግጅት ምዕራፎችም የተሳታፊ ልየታና ሥልጠና እንዲሁም ለአገራዊ መግባባት የተሻሉ አጀንዳዎችን መለየት የሚሉ ጉዳዮችን ያካተተ እንደሆነ ገልጸዋል።

የውይይት አጀንዳ የሚቀረጸው ከታችኛው ኅብረተሰብ ክፍል ፍላጎት እንደሆነ ጠቅሰው ከዚህ አኳያ ገለልተኛ የሕዝብ ወኪሎች በተገቢው መልኩ ይለያሉ ነው ያሉት።

ኮሚሽኑም መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ ሚዲያ ክፍሉን እያጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ የአገልግሎት ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የወሰንና ማንነት እንዲሁም በዕርቀ-ሰላም ኮሚሽኖች የተጠኑ የጥናት ሰነዶችን መረከቡን አንስተው ከሰነዶችም አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በግብዓትነት ይጠቀማል ብለዋል።

በተጨማሪ ኮሚሽኑ የራሱን ጥናት በማስጠናትም ከሌሎች ጥናቶች ላይ አዋህዶ ለምክክር እንደሚጠቀምበት ገልጸዋል።

“ምክክሩ በመንግሥትም ሆነ በሌላ የውጭ አካላት እንዲጠመዘዝና እንዲመራ አንፈቅድም” ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ከውስጥና ከውጭ ያሉ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ ምክክሩ ግቡን እንዲመታ እንሰራለን ብለዋል።

ከገንዘብ ጋር በተያያዘም ኮሚሽኑ በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር የትረስት ፈንድ በማስከፈት ማንኛውም ገንዘብ ድጋፍ ያደረገ የውጭ አካል ኦዲት ተደርጎ ገንዘቡ ምን ላይ እንደዋለ በግልጽ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።

ይህ ካለማንም ጣልቃገብነት የሚከወን ምክክር ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ አሻራ ጥሎ እንደሚያልፍም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት እንደ ስጋት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከልም በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶች፣ የዓለም ዐቀፉ ተለዋዋጭ ሁኔታና የሚዲያዎች የተዛባ መረጃዎች ሥርጭትን ለአብነት ጠቅሰዋል።

አገራዊ ምክክሩ በሦስት ዓመታት መጨረሻ ጠንካራ ውጤት እንደሚያመጣ ያላቸውን ተስፋ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።