አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ዘመናዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት መዘርጋት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው አሉ

ሰኔ 21/2014 (ዋልታ) ዘመናዊ የግጭት መከላከልና አፈታት ሥርዓት መዘርጋት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።

ምክር ቤቱ የብሔራዊ ግጭት መከላከልና ሰላም ግንባታ ስትራቴጂ ሰነድ በማዘጋጀት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከረ ነው።

አፈ ጉባኤው በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ዜጎች በማንነታቸው ብቻ እየሞቱ መሆኑን አንስተው ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ዘመናዊ የሆነ የግጭት መከላከልና አፈታት ስልትን መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የምክር ቤቱን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰን እና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴን በአዲስ መልክ በማደራጀት የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱ ተነግሯል፡፡

ምክር ቤቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር አንዱ በሕዝቦች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች ላይ ውሳኔ በመስጠት በሕዝቦች መካከል በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት እንዲኖር ማስቻል ነው።

በመስከረም ቸርነት