አፍሪካውያን ለኢትዮጵያ እውነተኛ ድጋፍ እያደረጉ ነው – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

ኅዳር 14/2014 (ዋልታ) በዓለም ዙሪያ ምዕራባውያንን ለመቃወምና ኢትዮጵያን ለመደገፍ እየተካሄዱ ባሉ የድጋፍ ሰልፎች አፍሪካውያን በተለይ ጎረቤት አገሮች ለኢትዮጵያ እውነተኛ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ።

ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለኢፕድ እንዳስታወቁት፤ ሰሞኑን በተለያዩ የዓለም አገራት በተጠራው ሰልፍ ላይ በርካታ አፍሪካውያን በተለይ ጎረቤት አገሮች ለኢትዮጵያ እውነተኛ ድጋፋቸውን አሳይተዋል።

በውጭ አገር የነበረው እንቅስቃሴ እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ በማለት ከ27 በላይ በሚሆኑ የአውሮፓ ከተማዎች አፍሪካውያንን በተለይ ጎረቤት አገራት ኤርትራውያን፣ ኬንያውያንና የሶማሊያ ዜጎችና የኢትዮጵያን ወዳጆችን ጨምሮ በጋራ ወጥተው ኢትዮጵያን አትንኩ፤ እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ ሰብስቡ የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸው የኢትዮጵያ ጉዳይ የአፍሪካ መሆኑን አመላካች ነው ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገር ቤት ያሉ ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው የሚያነሱትን ጥያቄ በመረዳት የኅልውና ዘመቻውን መደገፋቸው በጉልህ ታይቷል።