ኢራናውያን አዲስ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ድምጽ እየሰጡ ነው

ሰኔ 11/2013 (ዋልታ) – ሐሰን ሩሃኒን የሚተኩ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ኢራናውያን ዛሬ ድምጽ እየሰጡ ነው።

በምርጫው ከሕዝብ በተሰበሰበ አስተያየት መሠረት የፍትህ ሥርዓቱን በበላይነት የሚመሩት ወግ አጥባቂ የሺአ መሪ ኢብራሂም ራይሲ ያሸንፋሉ ተብሎ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

የቀድሞው ማዕከላዊ ባንክ ገዥ አብዶልናስር ሄማቲ ተቀናቃኛቸው መሆናቸውም ተገልጿል።

ሐይማኖታዊው መሪ አያቶላህ አሊ ካሜኒ ዛሬ ማለዳ ዋና ከተማዋ ቴህራን ውስጥ ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ ሰዎች እንዲመርጡ አበረታተዋል።

“እያንዳንዱ ድምጽ ዋጋ አለው፤ ይምጡና ፕሬዝዳንትዎን ይምረጡ፤ ይህ ለአገርዎ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ለዘብተኛው ሩሃኒ ለሁለት ተከታታይ አራት ዓመታት የሥልጣን ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸውን በድጋሚ መወዳደር እንደማይችሉ ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል።