ኢሬቻ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ እሴት ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

መስከረም 20/2015 (ዋልታ) ኢሬቻ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ እሴት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከተማ እየተከበረ ባለው አራተኛ የኢሬቻ ፎረም የዋዜማ ዝግጅት ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባህሉ ከኦሮሞ ውስጥ ይመንጭ እንጂ ስለአብሮነት የሚሰበክበት፤ አብሮነት ከንግግር ባለፈ በተግባር የሚኖርበት መሆኑን እያሰረፀ የመጣበት ነው ብለዋል፡፡

ኦሮሞ በኢሬቻ ፈጣሪን ያመሰግንበታል እንጂ ተፈጥሮን አያመልክም ያሉት ከንቲባዋ ዋቃ ኡማ ኡመማ ማለት የተፈጥሮ ፈጣሪ ፤ ተፈጥሮን የፈጠርክ አምላክ ምስጋና ይገባሃል፤ ውሃውን የደፈረሰውን አጥርተህልናልና እናመሰግናለን ፤ እኛም ታርቀን ሰላም ሆነን፤ ገራ ቁልቁሉ ሆዳችን ንፁህ አድርገን ተሰብስበናልና እባክህ ንፁህ አድርገን ታረቀን በማለት በባህላዊ መንገድ ልመናቸውን የሚያቀርቡበት እሴት ነው ብለዋል፡፡

ይህ እሴት የመላው ኢትዮጵያውያን እሴት ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች በገዳ ሥርዓት ምክንያት ከእኛም አልፎ ለዓለም ህዝብ ያስተዋወቀን ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በጠቅላላው የኢሬቻ በዓል ማክበር ከጀመረበት 4 ዓመት ወዲህ ባህሉን ለማሳደግና ግንዛቤ ለመፍጠር ሰፋፊ ስራዎችን መስራቱንም አውስተዋል፡፡