ኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ልዩነት የምታይባቸውን ጉዳዮች መፍታት እንደሚገባ ተገለፀ

አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ

የካቲት 3/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን ለዘመናት የዘለቀ ሁለንተናዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ልዩነት የምታይባቸውን የድንበር እና የኅዳሴ ግድብ ጉዳዮች ለመፍታት ተቀራርቦ መስራት ተገቢ እንደሆነ በሱዳን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ገለፁ፡፡

አምባሳደር ይበልጣል ከሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር አሊ አል ሳዲቅ አሊ በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም መተማ-ገለባት የድንበር ኬላ ለዜጎች እንቅስቃሴ ክፍት እንዲደረግ፣ ወደ አገራቸው ለመመለስ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን በኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተጣለው የመውጫ ክፍያ እንዲሰረዝ ወይም የኢትዮጵያዊያን ኑሮና ገቢ ሁኔታ ያማከለ እንዲሆን ጥያቄ አቅርበዋል።

የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት በልዩ ሁኔታ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የመተማ-ገለባት ድንበር እንዲከፈትና የመውጫ ቪዛ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

በሁለቱ አገራት መካካል ያለውን ግንኙት ካለበት ደረጃ ለማሻሻል የሚስተዋሉ ጅምር እንቅስቃሴዎችን ለማስቀጠል፣ በድንበር እና በኅዳሴ ግድብ ጉዳይ እንዲሁም በሌሎች ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ ተቀራርቦ ለመነጋገርና የጋራ መፍትሔዎችን ለማበጀት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።