ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በመከላከያ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር አለባቸው


ግንቦት 25/2014 (ዋልታ)
ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በመከላከያ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
በኡጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለምፀሀይ መሰረት ከኡጋንዳ መከላከያ ሚኒስትር ቪንሰንት ሲምፒጃ ጋር በቀጠናዊ ፀጥታና ሰላም ጉዳዮች እንዲሁም በሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
በውይይቱም አምባሳደር አለምፀሀይ አገራቱ ሽብርተኝነትንና ፅንፈኝነትን በጋራ በመዋጋት፣ በደቡብ ሱዳንና በሱማሊያ ሰላም ለማምጣትና በቀጠናው ያላቸውን ሚና በትብብር ለማጠናከር የኢትዮጵያን ዝግጁነት ገልፀዋል፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል በመከላከያ ትብብር ዘርፍ የተደረጉ ስምምነቶች የሚኖራቸውን አስተዋጽዎ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያና ኡጋንዳ ለዘመናት የቆየ በተለያዩ ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸውና በአፍሪካ አጀንዳዎችና በፓን አፍሪካዊ እሳቤዎች ተመሳሳይ አቋሞችን የሚያራምዱ አገራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኡጋንዳ መንግሥትም ለግንኙነቱ ትልቅ ቦታ ይሰጣል፤ በተለይም በመከላከያ ዘርፍ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት ሚኒሰትሩ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ኡጋንዳ ፓን-አፍሪካዊ ዕሳቤን የሀገራዊ ፖሊሲዋ አካል አድርጋ የምትቀበል ሀገር እንደመሆኗ አብሮ ለማደግና ለመበልፀግ ሰላማዊ ለሆኑ አፍሪካዊ ወንድሞቻችን በሯ ክፍት ቢሆንም የኢትዮጵያን ጥቅም የሚፃረሩና ድብቅ ሴራዎችን አንግበው ለሚንቀሳቀሱ አካላት ምንም አይነት ቦታ እንደሌላቸው አጽንኦት መስጠታቸውን ኤምባሲው አስታውቋል።
አገራቱ በመከላከያ ትብብር ዘርፍ ስር በመረጃ ልውውጥ፣ ሚሊተሪ ስልጠና፣በጥናትና ምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና ቴክኒካዊ ድጋፍ በመሳሰሉት ያላቸውን ትብብር አጠናክሮ ለመቀጠል በቀጣይ በቴክኒካል ቡድን ደረጃ ውይይቶችን በአዲስ አበባ ለማድረግ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡