ግንቦት 28/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያን የሚመስል የፀጥታ ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የምስጋና እና ዕውቅና መርኃ ግብር ዛሬ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር የሰላም ጊዜ በየአካባቢው በጦርነቱ በየግንባሩ ደፋ ቀና ለሚለው ፌዴራል ፖሊስ ቀን የእንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
ሕዝብ ሰላም ውሎ የሚያድረው በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ልፋትና ተጋድሎ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላምን ዋጋ ብንገነዘብ ወደ ግጭት አንገባም፤ ለሀገር ሰላምና ብልፅግና መሰረት ሰላም በመሆኑ የፀጥታ ተቋማትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
ፀጥታና ሰላም ለማረጋገጥ የሚጋደሉ ፖሊሶችን ማክበር ተገቢ ነው፣ አነስተኛ ደመወዝ እየተከፈላቸው ለሀገር ከፍተኛ ዋጋ የሚከፍል ፖሊስ ነው ሲሉም አክለዋል።
የኛ ዓላማ በዕውቀት በዕውነት ለሕዝብ የሚሰሩ ተቋማትን ማጠናከር ነው፣ የፀጥታ ተቋማትን የማጠናከር ሥራ የፌዴራል ፖሊስ ምሳሌ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ 24 ሰዓት የሚሰራ ኃይል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ንፁሃን ዜጎች ከተኩላዎች እንድትጠብቁ አሳስባለሁ ብለዋል።
ፖሊስን በማዘመን ታሪክ ራስ መኮንን ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ገልፀው ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለስላሴ ዘመን እየጎለበተ መምጣቱን ገልፀዋል።
ፖሊስ ሀገር በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ምስረታም ሚናው ጉልህ ነበር ብለዋል።