ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን አሸናፊነት አረጋግጠናል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተናገሩ

የታኅሣሥ 24/2014 (ዋልታ) የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ተገደን ባካሄድነውን ጦርነት ኢትዮጵያዊያን ከጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን አሸናፊነት አረጋግጠናል ሲሉ ተናገሩ፡፡

የሲዳማ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ነው፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በመድረኩ አሸባሪው ትሕነግ የተቃጣብንንና ያለፍላጎት ተገደን ያካሄድነውን ጦርነት ክብሩንና ልዕልናውን ላለማስደፈር በቆረጠው የአገራችን ሕዝብና ጀግናው የመከላከያ ኃይላችን በመቀናጀት የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን ቅስም ሰብረናል ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ድሉን የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍና የምጣኔሃብት ጉዳቱ እንዲያገግም በትኩረት በመስራት ድሉን መድገም ይገባል ማለታቸውን ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡