ኢትዮጵያውያን በአድዋ ያሳዩነትን ዘመን ተሻጋሪ ድል የአሁኑ ትውልድ ግድቡን በማጠናቀቅ እንዲደግመው ጥሪ ቀረበ

የካቲት 21/2013 (ዋልታ)– የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በአሜሪካ ከ15 ስቴቶች ለተውጣጡ የዳያስፖራ ወገኖች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የግድቡ ግንባታ 78 በመቶ መጠናቀቁን የገለጹት ሚኒስትሩ ስራውም በከፍተኛ የአገራዊ ፍቅር ስሜት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ማንኛውም አይነት የቅኝ ግዛትና ኢፍትኃዊ ውል እንደማትቀበል፣ የግርጌ ተፋሰስ አገራትን ሳትጎዳ የተፈጥሮ ኃብቶቿን ማልማቷን እንደምትቀጥልም ተናግረዋል።

ይህን የአገር ኩራት ፕሮጀክት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖች በቻሉት ሁሉ በመደገፍ የቀድሞ ወገኖች በአድዋ ድል ያስመዘገቡትን አንጸባራቂ ድል እንዲደግሙት ጥሪ አስተላልፈዋል።

በአሜሪካ የኢፌዴሪ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው የህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃትና ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ በረከቶች እንደሚኖሩት ገልጸዋል።

ኤምባሲው በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር የጀመረውን የገንዘብ፣ የአድቮኬሲ እና የሙያ ድጋፎችን የማስተባበር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የውይይቱ ተሳተፊዎች ግድቡ እስኪጠናቀቅ በበለጠ የአገር ፍቅርና ወኔ ሁሉን አቀፍ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል መግባታቸውን በአሜሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲው የተገኘነው መረጃ ያመላክታል።