ኢትዮጵያውያን አብሮ የመኖር እሴታቸውን የሚሸረሽሩ ድርጊቶችን መመርመር አለባቸው ተባለ

ሚያዚያ 21/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያውያን የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴታቸውን የሚሸረሽሩ ድርጊቶችን በሰከነ መንገድ ማየት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ አገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ አመራር አባል ሙሉጌታ ደበበ (ዶ/ር) ገለጹ።

በግጭቶች ህይወታቸው የሚያልፈውና የሚጎዱት ንጹሃን ዜጎች እንጂ ከኋላ ሆነው አጀንዳ የሚሰጡ አካላት አለመሆናቸውንም ገልጸዋል።

ዶክተር ሙሉጌታ በጎንደር ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ ድርጊቱ ተደጋግፈውና ተቻችለው እየኖሩ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የማይወክል መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያውያን ተከባብረው በአንድነት የመኖር ማህበራዊ እሴታቸውን ለመሸርሸር የሚንቀሳቀሱ አካላትን በጋራ መመከት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ሃይማኖትና ብሔርን ሽፋን በማድረግ ግጭት የሚቀሰቅሱ ሃይሎች መጠቀሚያ ላለመሆን ነገሮችን ቆም ብለው ማሰብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ላላት የዳበረ የአገር ሽምግልና እና ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ትኩረት በመስጠት ችግሮች ሳይሰፉ መፍታት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም ብሔርና ሃማኖትን ሽፋን በማድረግ ግጭት መፍጠር አገርን ወደ ኋላ የጎተተ አካሄድ በመሆኑ ወቅቱ ውይይት የሚያስፈልግበት ወሳኝ ጊዜ መሆኑንም በአጽእኖት አንስተዋል።

በሃይማኖትና በብሔር በመሸሸግ ህዝብና አገርን ከመጉዳት ኋላቀር አካሄድ በመውጣት ሁሉም በጋራ የሚኖርባትን አገር መፍጠር አለብን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከህግ በላይ የሚሆን አካል ባለመኖሩ መንግስት ወንጀለኞችን ለህግ በማቅረብ አስተማሪ ርምጃ መውሰድ እንዳለበትም የኢትዮጵያ አገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ አመራር አባል ዶክተር ሙሉጌታ ጠቁመዋል።