ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ያለው ድጋፍ ጉዳት የደረሰበት ሕዝባችንን ለማቋቋም የሚያስችል ነው- ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) “መላ ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ጉዳት የደረሰበት ሕዝባችንን ለማቋቋም የሚያስችል ነው” ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለጹ።

የፍትህ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ጠበቆችና የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ጋር በመተባበር የ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እና የአይነት ድጋፍ ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስረክበዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በርክክብ ስነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት “ወራሪው ቡድን በሕዝባችን ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለው ድጋፍ ተጎጂዎች የደረሰባቸውን የልብ ስብራት ለመጠገን የሚያስችል ነው” ብለዋል።

“የፍትህ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎችና የጠበቆች ማኅበር ዛሬ ያደረጋችሁት ድጋፍም ለወገናችሁ ያላችሁ አጋርነት ማረጋገጫ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቃዱ ፀጋ በበኩላቸው “አሸባሪ ቡድኑ ያደረሰው መጠነ ሰፊ ጉዳትና ውድመት በአንድ ጊዜ አስተዋጽኦ ሊፈታ አይችልም” ብለዋል።

በመሆኑም መንግሥት፣ መላ ኢትዮጵያዊያን እና ረጂ ድርጅቶች የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራውን ለማሳካት በቀጣይ በጋራ ተረባርበን ልንሰራ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡