ኢትዮጵያ ለቀጠናውም ሆነ ለዓለም ሰላም እያበረከተች ያለው አስተዋፅኦ የሚደነቅ ነው – በሱዳን የካናዳ ኤምባሲ የፖለቲካል ተቀዳሚ ፀሃፊ

 

ኢትዮጵያ ለቀጠናውም ሆነ ለዓለም ሰላም እያበረከተች ያለው አስተዋፅኦ የሚደነቅ መሆኑን በሱዳን የካናዳ ኤምባሲ የፖለቲካል ተቀዳሚ ፀሃፊ ባሪ ፓርኪንሰን ተናገሩ፡፡

ፀሃፊው በአብየ ሰሜን ቀጠና ከሚገኙ የሚስሪያ ጎሳ መሪዎችና ከአካባቢው አስተዳዳሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የመሰረታዊ ፍላጎቶች እጥረት እንደ ውሃ ፣ ትምህርት ፣ የጤና አገልግሎት ፣ የመንገድና ሌሎች የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ጎሳ መሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡

ጸሃፊው ፓርኪንሰን በሰጡት ምላሽ በአካባቢው የሚስተዋል የመሰረተ ልማት እጥረቶችን ለመቅረፍ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚነጋገሩበት ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ ለቀጠናውንም ሆነ ለዓለም ሰላም እያበረከተች ያለውን አስተዋፅኦ አድንቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ 23ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ ወደ ቀጠናው ከተሰማራ ጀምሮ በአካባቢው የተረጋጋ ሰላም ለማስፈን እያደረገ ላለው ያልተቋረጠ ጥረት ጎሳ መሪዎቹ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የዲፍራ ላይዘን ኦፊሰር ብርጋዴር ጄኔራል ዋኘው አለሜ ፣ የሻለቃው ዋና አዛዥ ኮሎኔል ሃሰን አብደላ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው በተመድ የአቢዬ ጊዜያዊ የጸጥታ ኃይል (ዩኒስፋ) የስራ ሃላፊዎች መሳተፋቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡