ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ሰባት ሜዳሊያዎችን አገኘች

ግንቦት 1/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ሲካሄድ በቆየው የምሥራቅ አፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ሰባት ሜዳሊያዎችን በማግኘት አጠናቃለች።
ከሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ዘጠኝ አገራት የተሳተፉበት ውድድር ለአራት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ተካሂዷል።
በዚህ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድን ሁለት የወርቅ፣ ሁለት የብር እና ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን በአጠቃላይ ሰባት ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችሏል።
የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያ በወንዶች የነጠላ ውድድር በአትሌት ደራራ መኮንን የተገኘ ሲሆን ሁለተኛው የወርቅ ሜዳሊያ ደግሞ በሴቶች የቡድን ጨዋታ የተገኘ ነው።
ሁለቱ የብር ሜዳሊያዎች ደግሞ በሴቶች ነጠላ ውድድር ማርታ መሸሻ እና በወንዶች የቡድን ጨዋታ የተገኙ ናቸው።
ሦስቱ የነሐስ ሜዳሊያዎች ደግሞ በሴቶች ነጠላ ውድድር በሜሮን ጌታነህ እና በቤተልሔም ሲሳይ አማካኝነት የተገኙ ሲሆን ሌላኛው አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ደግሞ በወንዶች የነጠላ ውድድር በአትሌት ኤደን ተስፋዬ የመጣ ነው።
በዚህ ውድድር ጥሩ ተፎካካሪ የነበሩት የሞሪሽየስ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ሁለት ወርቅና ሁለት የብር ሜዳሊያ ማግኘት ችለዋል።
በውድድሩ በቡድን ሁለት ሀገራት በነጠላ ደግሞ ከአንድ እስከ ስምንተኛ ደረጃ የወጡ ስፖርተኞች ምሥራቅ አፍሪካን ወክለው በ2022 ዓ.ም በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ውድድር ላይ የሚካፈሉ ይሆናል።
በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያ በቡድን ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር በሁለቱም ጾታ ተካፋይ እንደሚሆኑ ኢዜአ ዘግቧል።