ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎት አላት – አቶ ደመቀ መኮንን

ሚያዚያ 08/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በሶስቱም ሀገሮች ተቀባይነት ያለው ስምምነት ላይ ለመድረስ በአፍሪካ ህብረት ማእቀፍ ስር የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን  ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ በአውሮፓ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጋር በበይነ መረብ በተካሄደው ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት ሶስቱ ሀገራት የአባይን ውሃ አጠቃቀም በተመለከተ ያላቸው አማራጭ በትብብር እና በአፍሪካዊ ወንድማማችነት ስሜት በጋራ መስራት ነው ብለዋል፡፡

ድርድሩን ስኬታማ ለማድረግና መተማመንን ለማጎልበት እ.አ.አ በጁላይ 2020 በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የቢሮ ስብሰባ ወቅት በተፈረመው መግባባት እና በወጣው መግለጫ መሰረት  በግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት እና ተያያዥ የውሃ አለቃቀቅ ጉዳዮች እና  ሁሉን አቀፍ የውሃ አጠቃቀም ስምምነቶችን ማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በቀጣዩ ሀምሌ ወር የሚደረገውን የሁለተኛ አመት ሙሌት አስመልክተው አቶ ደመቀ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ በቅን ልቦና ተነሳሽነቱን በመውሰድ ለግብጽ እና ለሱዳን ደብዳቤ ተልኳል፡፡

ሚኒስትሩ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ሁሉ አፍሪካዊ ሆነው ሳሉ ጉዳዩን ለፖለቲካ ጠቀሜታ ሲባል የሚያራምዱት አቋም ተቀባይነት የሌለውና ሁሉም በአጽንኦት ሊገነዘበው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንዳመላከተው አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ በፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም በጽኑ እንደምታምን ጠቁመው ሀገሪቱ ማንንም የመጉዳት አላማ የላትም ብለዋል፡፡

አክለውም በአባይ ወንዝ ላይ ግብጽና ሱዳን የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን መልሰው በማምጣት ሙሉ በሙሉ የመጠቀም ፍላጎት ማሳየታቸው ኢትዮጵያ በድርድሩ ተስፋ ቆርጣ እንድትወጣ በማድረግ የውሃ ሀብቱን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ፍላጎት በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም ነው ያሉት፡፡