ኢትዮጵያ እና ህንድ በማኅበራዊ ጉዳዮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ

ነሐሴ 3/2014 (ዋልታ) የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከህንድ የማኅበራዊ ፍትሕ እና ማብቃት ሚኒስትር ቬሬንድራ ኩማር (ዶ/ር) ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የማኅበራዊ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በኒውደልሂ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ስትራቴጂክ ወደ ሆነ አጋርነት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ባለስልጣናቱ ተስማምተዋል።

በአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ የወጣቶች ስልጠና እንዲሁም የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማገዝ በሚቻልበት ጉዳይ ላይም ተወያይተዋል።

በተለይ አካል ጉዳተኞችን ማብቃት፣ የእፅ ተጠቃሚነትን መከላከል እና መልሶ ማቋቋም እንዲሁም አረጋውያንን በተመለከቱ በልዩ ሁኔታ ለመስራት ተስማምተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአረጋውያን ማዕከል ለማቋቋም አዲስ ፕሮጀክት ቀርፆ እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ሚኒስትሯ ማዕከሉን ለማቋቋም ከህንድ ትልቅ ልምድ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

የህንድ መንግሥት በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የሚያደርገውን ድጋፍ አድንቀው ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት የሚሰጠውን የትምህርት እድል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የህንዱ የማኅበራዊ ፍትህ እና ማብቃት ሚኒስትር ቪሬንድራ ኩማር (ዶ/ር) በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራቸው ይህን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ መንግስት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያደረገው ጥረት መንግሥት ለጾታ እኩልነት ለሰጠው ትኩረት ማሳያ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።