ኢትዮጵያ እና የኮሪያ ዓለም ዐቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

የካቲት 29/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ እና የኮሪያ ዓለም ዐቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የ20 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የእርዳታ መግባቢያ ሰነዱ የተፈረመው የኮሪያ ዓለም ዐቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የ2022 የድጋፍ መርሃ ግብር ማስፈጸሚያ ማዕቀፎችን፣ የኢትዮጵያን የአስር አመት እቅድ እና ዘላቂ የልማት ግቦችን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያን የልማት ጥረት ለማሳካት በሚያግዝ መልኩ ነው ተብሏል።

የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ለሁለት ፕሮጀክቶች የሚውል ሲሆን የመጀመሪያው ፕሮጀክት በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ምርትና ምርታማነትና ለማጎልበት፣ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግና የተደላደለ የገበያ እና የንግድ ትስስርን በማዳበር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ሁለተኛው ፕሮጀክት በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን ማኅበራዊ ትስስር እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን ለማጎልበት፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መቋቋምን ለመፍጠር፣ ቀጣይነት ያለው የኑሮ መሻሻልን ለማሳደግ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያግዝ መሆኑ ተነግሯል፡፡