ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ጋር ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤን ለማስተናገድ ስምምነት ተፈራረመች

ሐምሌ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ጋር የዓለም አቀፉን የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ስብሰባ ከሀምሌ 15-19 ቀን 2016  ለማስተናገድ የሚያስችል የአስተናጋጅ ሀገር ስምምነት ተፈራረመች።

በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ እና የመንግስታቱ ድርጅት የምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሃፊ ሊ ጁንዋ ስምምነቱን ፈርመዋል።

አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ኢትዮጵያ ስብሰባውን ማስተናገዷ የተባበሩት መንግስታት አሰራርን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እና የባለብዙ ወገን ትብብሮች እንዲጠናከሩ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ምክትል ዋና ጸሃፊዋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ስብሰባውን ለማስተናገድ ያላትን ቁርጠኝነት እና ሚና አድንቀዋል። ሁለቱ ወገኖች ለዘላቂ ልማት ግቦች አጀንዳ ማስፈጸሚያ ፋይናንስ ለማሰባሰብ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማነሳሳት ጉባዔው ያለውን ጠቀሜታ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ሦስተኛውን የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ አስተናግዳለች። ጉባዔው ለዘላቂ ልማት ግቦች ፋይናንስ ለማፈላለግ አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ማዕቀፍ ያስቀመጠውን የአዲስ አበባ የድርጊት መርሃ ግብር ማፅደቁ ይታወሳል።

ከሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ስብሰባ የአዲስ አበባ የድርጊት መርሃ ግብርን አፈፃፀም እንደሚገመግም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

እንዲሁም በቀጣይ ዓመት በስፔን ለሚካሄደው አራተኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።