ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የሁለትዮሽ የባለብዙ ወገን ትብብር ለማጠናከር እየሰራች መሆኗ ተገለጸ

አምባሳደር ተሾመ ቶጋ

ጥቅምት 5/2015 (ዋልታ) በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተውን የኢትዮጵያና የቻይና ሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ያላቸውን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ገለጹ።

አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት ከ50 ዓመታት በላይ የዘለቀና በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ አድማሱን እያሰፋና እየተጠናከረ መጥቷል ብለዋል።

ቻይና በኢትዮጵያ በበርካታ የልማት መስኮች ላይ ንቁ ተሳታፊ የሆነች ወዳጅ አገር መሆኗን ጠቅሰው ቻይና የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴዎች በፋይናንስና በቴክኒክ ድጋፍ እያገዘች መሆኗን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በመንገድ መሰረት ልማት፣ በኃይል ልማት፣ በትራንፖርትና የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት በሰጣቸው በሌሎች ድኅነት ተኮር የልማት ሴክተሮች ላይ ድጋፍ ማድረጓን ጠቅሰዋል።

ጎን ለጎንም የቻይና ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በማኑፋከቸሪንግ በተለይም ደግሞ በጨርቃ ጨርቅና በፋርማሲዩቲካል ዘርፎች ላይ ተሳትፏቸው እየጎለበተ መምጣቱን ገልጸው አጠቃላይ ግንኙነቱ እየተጠናከረ መሆኑን ተናግረዋል።

የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን ተሳትፎ የበለጠ ለማጠናከር ኤምባሲው በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ አገሪቱ ከያዘችው የአስር ዓመት መሪ እቅድ ጋር በማሰናሰል የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች በቻይና የገበያ እድል እንዲያገኙ ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም የኢትዮጵያ ቡናና ሰሊጥ በቻይና ገበያ ትልቅ ድርሻ እየያዙ መሆኑን ጠቁመው ሌሎችም ምርቶች ድርሻ እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ደግሞ የተለያዩ አትክልት ምርቶችና የሥጋ ምርቶች የቻይና ገበያን እንዲቀላቀሉ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸው በኢትዮጵያ በኩል ምርቶቹ ላይ እሴት መጨመር ከተቻለ ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት ይቻላል ነው ያሉት።

ቻይና የደረሰችበትን የእድገት ተሞክሮ ለመቀመር የሚያስችል በቴክኖሎጂና በሳይንስ ዘርፍ የልምድ ልውውጡን ለማጠናከር የሚያስችሉ የትምርትና የሥልጠና ድጋፎችም እየተጠናከሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳለጥም አንድም በኢንቨስትመንት በሌላ በኩል ደግሞ በሁለትዮሽ ግንኙነት ማዕቀፍ የትምህርትና ሥልጠና ሥራዎች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ አሁን በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ ከገጠማት ጦርነት ጋር በተያያዘ ጉዳዩ የውስጥ ጉዳይ እንደሆነና ኢትዮጵያ እራሷ መፍታት እንዳለባት ቻይና በመርህ ላይ የተመረኮዘ አቋም ስታንጸባርቅ መቆየቷን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ያም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት በሚካሄደው የሠላም ጥረት መፈታት አለበት የሚል አቋሟን ያለምንም መዛነፍ መግለጿንም ጠቅሰዋል።

ይህንንም አጋርነቷን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በአንጻሩ በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ኢትዮጵያና ቻይና ያጋራ በሆኑ የአየር ንብረት፣ ሽብርተኝነትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጓዳኝም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት በማስፈን ያላትን አበርክቶ ከግምት በማስገባት በአካባቢውም ሆነ በመላው አፍሪካ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ከቻይና ጋር በቅርበት መሥራቷን ትቀጥላለች ብለዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!