ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) “ኢትዮጵያ ጤናማ ምድር እንዲኖር ፍትሐዊ ድርሻዋን እየተወጣች ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
“እየጨመረ ለመጣው የምድር ከባቢ አየር ፈተናዎች ራሳችንን ዝግጁ ማድረግ አለብን” ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት “ስቶክሆልም +50” በሚል ስያሜ የአካባቢ ጥበቃን አስመልክቶ በስዊድን ስቶክሆልም ያዘጋጀው ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል።
“ስቶክሆልም +50” የዓለም አካባቢ ጥበቃን በማስመልከት በስዊድን የተካሄደውን ጉባኤ 50ኛ ዓመት በማስመልከት የተዘጋጀ ስብስባ ነው።
“ስቶክሆልም +50” ጉባኤን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት “ጉባኤው ልማትና ከባቢ አየርን በማስተሳሰር የሚካሄድና ከምድር ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ለማስቀጠል በድጋሚ ቃል የምንገባበት ነው” ብለዋል።
ጉባኤው የምድር ከባቢ አየር የምታስተናግዳቸው ፈተናዎችና ኢ-ሚዛናዊ እድገት እየጨመሩ በመጡበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑ በጣም ወሳኝ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
“ለሁላችንም ጤናማ የሆነች ምድር መፍጠር ከፈለግን በትብብር መስራት ይኖርብናል፤ መጪውን ጊዜ የተሻለ ለማድረግ አሁን ያሉንን አስተሳሰቦች መለስ ብለን መመልከት ያስፈልጋል” ብለዋል።
እ.አ.አ በ1972 በስዊድን በተካሄደው የዓለም አካባቢ ጥበቃ ጉባኤ “ስቶክሆልም መግለጫ” በሚል ስያሜ ስምምነት የተደረሰባቸውን ሀሳቦች በነጠላና በጋራ ምን ያህል ተግባራዊ ተደርገዋል የሚለውን ጉዳይ ማጤን እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።