ኢትዮጵያ 210 ሚሊየን ዶላር ከዓለም ባንክ በድጋፍ አገኘች

ግንቦት 30/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውሃ በብዛት በሚገኝባቸው ዝናብ አጠርና ቆለማ በሆኑ አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃን ለማልማትና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል 210 ሚሊየን ዶላር ከዓለም ባንክ በድጋፍ አገኘች፡፡

ገንዘቡ በኢትዮጵያ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃን በማልማት ለመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም ለመስኖ ልማት ለማዋል ለተቀረጹ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስቴር በ5 ዓመታት ውስጥ የሚተገበሩ ሲሆን ዝናብ አጠርና ቆላማ አካባቢ የሚኖሩ የሀገሪቱን ዜጎች ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

ይህንኑ አስመልክቶ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ከዓለም ባንክ ልዑክ ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን የድጋፍ ስምምነቱ በገንዘብ ሚኒስቴር ከተፈረመና በሀገሪቱ ፓርላማ ከፀደቀ በኋላ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል፡፡