ኢትዮ ቴሌኮም ከነበረበት እዳ 67 በመቶ መክፈሉን አስታወቀ

ነሃሴ 13/2013 (ዋልታ) – ኢትዮ ቴሌኮም ለማስፋፊያ ስራ ከተበደረው 2.3 ቢሊየን ዶላር 1 ነጥብ 56 ቢሊየን ዶላር ከፍሎ ማጠናቀቁን አስታወቀ ።
በዚህም 67 በመቶ የተከፈለ ሲሆን ቀሪው 33በመቶ ወይም 881 ሚሊየን ዶላር እዳ ለመክፈል እስከ ፈረንጆቹ አመት 2029 ጊዜ እንዳለው ተገልጿል።
ባለፋት ሶስት አመታት ተቋሙ ከነበረበት እዳ 40 በመቶውን መክፈል መቻሉንም ነው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬ ህይወት ታምሩ ተናግረዋል።
ኩባንያው በቀጣይ አመት በከፊል ወደ ግል የሚዞር በመሆኑ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ሊያደርጉት የሚችሉ አዳዲስ ፈጣን እና ተደራሽ የሆኑ አገልግሎቶችን በ2014 ለደንበኞቹ ለማቅረብ ዝግጅት ማጠናቀቁ ተነግሯል።
ተቋሙ ላለፋት ሶስት አመታት ሲጠቀምበት የነበረውን ብሪጂ የተሠኘውን እስትራቴጂ እስከ 2016 ለመጠቀም ከልሶ ወደ ስራ መግባቱን ተገልጿል።
በዚህም መሠረት የ2014 የቢዝነስ እስትራቴጂውን ቀርጿ ገምግሞ ወደስራ መግባቱን ገልጿል።
እስትራቴጂው ኢትዮ ቴሌኮም ተመራጭ እና የደንበኞችን ፍላጎት የሚያረካ ትርፋማ ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችል ሆኖ መቀረፁን ነው የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ የገለፁት።
ተቋሙ በ2014 በጀት አመት ተጨማሪ 13 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ለማስገኘት አቅዶ እየሠራ መሆኑን ተገልጿል።
ይህም ካለፈው አመት ገቢ 24 በመቶ ጭማሪ ያለው ሲሆን በበጀት አመቱ በጥቅሉ 70 ቢሊየን ገቢ ለማግኘት ተቋሙ አቅዷል።
ለዚህም ይረዳው ዘንድ 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ተጨማሪ ደንበኞችን በማፍራት 64 ሚሊየን ደንበኞችን ለማፍራት እየሠራ መሆኑም ተመላክቷል።
ይህም ካለፈው አመት 14 በመቶ እድገት ማሳየቱን ነው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬ ህይወት የተቋሙን የ2014 ቢዝነስ እስትራቴጂን ለጋዜጠኞች በገለፁበት ወቅት ያስታወቁት።
ለደንበኞቹ በፖኬጅ አገልግሎቶቹ ላይ 20በመቶ ቅናሽን ጨምሮ አዳዲስ ቀላል እና ፈጣን ፖኬጆችን ለደንበኞቹ ለ2014 መዘጋጀቱንም አንስተዋል።
በተጨማሪም ለመጪው አዲስ አመት አደይ አበባ የተሠኘ ለአንድ ወር የሚቆይ ጥቅል 44በመቶ ቅናሽ በማድረግ ተቋሙ ማቅረቡም ተገልጿል።
(በድልአብ ለማ )