ኢንስቲትዩቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ከባድ ዝናብና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል አሳሰበ

የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

ሰኔ 27/2014 (ዋልታ) የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ እርጥበት አዘል አየር በአጭር ጊዜ ተጠናክሮ በሚቀጥሉት ቀናት ከባድ ዝናብ በመፍጠር ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

በኢንስቲትዩቱ የአየር ሁኔታና የአየር ጸባይ ትንበያ ዳይሬክተር ጫሊ ደበሌ እንደገለጹት ከደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው እርጥበት አዘል አየር ካለፉት ሳምንታት በበለጠ በቀጣዮቹ ሳምንታት ሊጠናከር እንደሚችል ትንበያዎች ያሳያሉ።

በዚህም የጎርፍ አደጋ ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ አደጋ እንዳይፈጠር ከወዲሁ የመከላከል ሥራ ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ ወንዞችና ተዳፋታማ አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተጠናከረ የጥንቃቄ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በተለይ በከፍተኛ ቦታዎችና፣ በደጋ አካባቢ የሚዘንበው ዝናብ በዝቅተኛ አካባቢዎች ላይ የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመካከለኛ እና ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች እና በዝቅተኛ ቦታዎችም ላይ በአጭር ጊዜ የሚጥለው ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ ቦዮችን በመጥረግና በመክፈት፣ የውሃ መውረጃ በማዘጋጀት ጎርፍ ወደ ቤትና የእርሻ ማሳ እንዳይገባ ቅድመ ዝግጅት ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አልፎ አልፎ የሚያጋጥመው የመብረቅ አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ኅብረተሰቡ የራሱን ጥንቃቄ መውሰድ አለበት ብለዋል።

በዚህም በአብዛኛው የክረምት ተጠቃሚ ከሆኑት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች በስተቀር ሌሎች አካባቢዎችም ከመካከለኛ እስከ ከባድ ዝናብ ሊያገኙ ይችላሉ ሲሉ ጠቁመዋል።

ከሰኔ ወር በተሻለ መልኩ በሐምሌ ወር የተጠናከረ የዝናብ መጠንና ስርጭት ሊኖር ይችላል ብለዋል።

በሰሜን፣ ምስራቅ እና መካከለኛ የሀገሪቱ አካባቢ ላይ መደበኛ የዝናብ ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ትንበያዎች እንደሚያሳዩ ተናግረው ዝናቡ ለግብርና፣ ለውሃ ሃብትና ለሌሎችም ሥራዎች በጎ ጠቃሜታ ስላለው ኅብረተሰቡ በአግባቡ ሊጠቀምበት እንደሚገባ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት የዝናቡ ሁኔታ ወደ ሰሜን፣ ሰሜን ምስራቅና ምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል።

በዚህም በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ ዝናብ በአንዳንድ የምስራቅ አማራ፣ ምዕራብ አማራ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች መመዝገቡን ጠቁመዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW