ኢክናስ በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ስቴፋን ዮቢን የፈጸሙትን ድርጊት አወገዘ

ነሐሴ 3/2014 (ዋልታ) በካናዳ የሚገኘው የኢትዮ-ካናዳውያውያን ኔትወርክ ለማኅበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) በኢትዮጵያ የካናዳው አምባሳደር ስቴፋን ዮቢን በቅርቡ ከአሻባሪው ሕወሓት ጋር “ለሰሜኑ ግጭት ፖሊተካዊ መፍትሄ ማፈላለግ” በሚል ሽፋን ያደረጉትን ያልተገባ ግንኙነት እንደሚያወግዝ ለካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜለኒ ጆሊ በጻፈው ግልጽ ደብዳቤ አሳውቋል።

ኢክናስ በጻፈው ደብዳቤው እንደገለጸው አምባሳደሩ የተገናኟቸው የሕወሓት አሸባሪ ቡድን አመራሮች ለጦርነቱ መከሰት ምክኒያት ለሆነው ለሰሜን እዝ ጥቃት ኃላፊነት የሚወስዱ ብቻ ሳይሆኑ በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች ለተፈጠሩት የሰው እና የንብረት መጥፋቶች ምክንያት መሆናቸውን ገልጿል።

ቡድኑ ህጻናትን በግድ መልምሎ ለጦርነት እንዲሰማሩ በማድረግ እንዲሁም ‘ልጆቻችንን ወደ ጦር ግንባር አንልክም’ ያሉ ወላጆችን በማሰር እና በማሰቃየት ወንጀል ሲፈጽም መቆየቱን በተለያዩ ገለልተኛ እና ታማኝ በሆኑ አካላት የተሰሩ ሪፖርቶች ማመልከታቸውን ኢክናስ አስታውሷል።

ከነዚህ የዓለም አቀፍ የጦር ወንጀሎች በተጨማሪ አሸባሪ ቡድኑ በእረፍት ላይ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልእኮ አባላት የሆኑ ወታደሮችን በመመልመል በጄኔቫ የጦር እስረኞች ኮንቬንሽን መሰረት የዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ስለመፈጸሙን በደብዳቤው ገልጿል።

ካናዳ እስካሁን በጦርነቱ ዙሪያ ያላት አቋም እና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያላት ግንኙነት ለዴሞክራሲ እሴቶች፣ ደንቦች እንዲሁም መርሆች ጠንካራ አቋም እንዳላት ማንጸባረቁን ገልጿል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ካናዳ የምታደርገውን ድጋፍ ያደነቀው የኢክናስ ደብዳቤ፤ በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ዮቢን በመቀሌ ከሕወሃት አመራሮች ጋር ያደረጉት ያልተገባ ግንኙነት እጅግ አሳፋሪና የሚወገዝ መሆኑን አመልክቷል።

በተጨማሪም አምባሳደሩ በመቀሌ ያደረጉት ድርጊት ካናዳ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት የምታደረገውን ጥረት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ፍትሃዊ፣ እርስ በርስ በመከባባር ላይ የተመሰረት ወዳጅነት እና ያቆየችውን መልካም ስም የሚጎዳ ነው ሲል ገልጿል።

በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች የተጋራው የአምባሳደሩና የአሸባሪ ቡድኑ አመራሮች ፎቶ በመላው አለም የሚገኙ ኢትየጵያውያንን ያሳዘነ ተግባር ነው ያለው ኢክናስ፤ የአሸባሪ ቡድኑ አመራሮች በአፋር፣ ትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ለተከሰቱ የጦር ወንጀሎች፣ ሴቶች እና ህጻናት መደፈር እንዲሁም ለንጹሐን ሞት ተጠያቂ እንደሆኑ አፅንኦት ሰጥቶ አስረድቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት መቀሌን ለጎበኙ አምባሳደሮች እና ልዩ መልእክተኞች የሰላም ድርድር የሚካሄደው በአፍሪካ ህብረት በኩል ብቻ መሆኑን በግልጽ ቢያስረዳም ይህ የዲፕሎማሲ መንገድ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ተተርጉሞ የአፍሪካ ህብረትን እና የኢትዮጵያን መንግስት ልአላዊነትን አሳንሶ በማየት በህግ አሸባሪ የተባለን አካል ህጋዊ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ትክክል አለመሆኑን አስገንዝቧል።

ካናዳ ሽብርተኞችን ደግፋ እንደማታውቅ ያመላከተው ደብዳቤው፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በእርቅ የተደገፈ፣ ህብረተሰቡን ያማከለ መንግስታዊ አካሄድ፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ስርአት እንዲጠናከር የካናዳ መንግስት ሊያግዝ ይገባል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።