ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የሙስና ወንጀሎችን በጋራ መከላከል ይገባል – ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

ግንቦት 16/ 2013 (ዋልታ) – የተወሳሰቡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል በጋራ መሥራት እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተቋቋመበትን 20ኛ ዓመት በማስመልከት ዛሬ ከ500 በላይ ለሚሆኑ የበጎ-ምግባር ባለቤቶች ሽልማትና እውቅና ሰጥቷል።

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በኢኮኖሚና በፖለቲካ መስኮች የሚፈጸሙት የሙስና ወንጀሎች በባህሪያቸው የተደራጁና የተወሳሰቡ በመሆናቸው የሁሉንም ክትትል ይጠይቃሉ።

በተለይም በኃላፊነት ላይ የሚገኙ አመራሮች በሚመሯቸው ተቋማት ለሙስና አጋላጭ የሆኑ አሠራሮችና ሥርዓቶችን ሊያስወግዱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሠራተኞችም በአቋራጭ መበልጸግን በማስወገድ ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ ሃብት በማፍራት እንዲያስመዘግቡ መክረዋል።

ፕሬዚዳንቷ ሙስና በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ የሚካሄደውን የፍርድ ሂደት ለኅብረተሰቡ ግልጽ በማድረግ  እንዲማርበት ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የሚደረገውን ትግል ሁሉም ካልተቀላቀለ ወንጀሉ ይበልጥ እየተባባሰ እንደሚሄድ ጠቁመዋል።

ሥነ-ምግባር ያለው አገልጋይ በሁሉም የሥራ መስክ መፈጠር እንዳለበትና ለዚህም ትውልዱን በመልካም ምግባር መቅረጽ እንደሚገባም ፕሬዚዳንቷ አስገንዝበዋል።

የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽነር ጸጋ አራጌ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በሥነ-ምግባር ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የሙስና ወንጀሎች ከመፈጸማቸው በፊት ለመከላከል ሥራ አጽንኦት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ የሙስና ወንጀል የሚፈጽሙ ግለሰቦች በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እንደሚጠናከር ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት።

ኮሚሽኑ በተለይም ከትምህርት ቤት ጀምሮ የሚሰጠውን የሥነ-ምግባር ትምህርት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።