ኢጋድ ለአካባቢያዊ ውህደት እንደሚሠራ ገለጸ


ሐምሌ 16/2013 (ዋልታ) –
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት (ኢጋድ) ለክፍለ አህጉራዊ ውህደት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አስታወቀ።
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ተቋሙ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ አጎራባች ሕዝቦች መካከል በጤና፣ ግብርና እና ሌሎች መስኮች መደጋገፍ እንዲኖር በማድረግ ክፍለ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት እንዲኖር እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አዋሳኝ በሆነው የማንዴራ ክልል የሚካሄዱ የልማት ሥራዎችን የጎበኙ ሲሆን፣ የሁለቱንም ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ድጋፎችን ለማንዴራ ክልል አስተዳዳሪ አሊ ሮባ አስረክበዋል።
ድርጅቱ ቀደም ሰል በኢትዮጵያ ለዶሎ አዶ እና ዶሎ ባይ ወረዳዎች ድጋፍ አድርጓል።
በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው፣ በድንበሮች አካባቢ የሚገኙ ሕዝቦችን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ለሰላም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢጋድ ላደረገው ድጋፍ ማመስገናቸውን በኬኒያ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።