ኤለን መስክ የምድራችን ቀዳሚ ሀብታሙ ሰው ሆነ

                             ኤለን መስክ

የቴስላ ኤሌክትሪክ መኪና እና የስፔስ ኤክስ የሕዋ ታክሲ ፈጣሪና ባለቤት ኤለን መስክ ባልተጠበቀ ፍጥነት የየዓለም ሀብታሙ ሰው ሆኗል።

መስክ በድንገት 1ኛ የዓለም ሀብታም ሊሆን የቻለው የቴስላ የአክስዮን ዋጋ ማክሰኞ ዕለት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ ሀብቱ ወደ 185 ቢሊዮን ዶላር በመመንደጉ ነው።

ከፈረንጆቹ 2017 ዓ/ም ጀምሮ የዓለም ቢሊዮነሮች ዝርዝርን ከላይ ሆኖ ሲመራ የነበረው የአማዞኑ ባለቤት ጄፍ ቤዞስ ነበር።

የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ኩባንያ ቴስላ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአክስዮን መጠኑ በማይታመን ደረጃ እየጨመረ መጥቶ ትናንት ረቡዕ 700 ቢሊዯን ዶላር እንደደረሰ ቢቢሲ ዘግቧል።

የኤለን መስክ ቴስላ የአክስዮን ፍላጎት ለመጨመሩ በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ከነዚህ አንዱ መጪው ዘመን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ብዙ አገራት ፖሊሲያቸው ለኤሌክትሪክ መኪና የሚስማማ መሆኑ አይቀሬ እንደሆነ በመታመኑ ነው።