ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ እንዳይጸድቅ ኢትዮጵያዊያን ተጽዕኖ ማሳረፍ አለባቸው ተባለ

መጋቢት 15/2014 (ዋልታ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ አዋጆች እንዳይጸድቁ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያን ተጽዕኖ ማሳረፍ ይችላሉና ተቃውሟቸውን ሊያሰሙ ይገባል አሉ።

በተለይም ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሆኑ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው የመምረጥ መብታቸው ተጽዕኖ እንዲያሳርፉ እንደሚረዳም ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ በሳምንቱ የተከናወኑ ዲፕሎማሲያዊ ሁነቶችን አስመልክቶ በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያን ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ እንዳይጸድቅ ተቃውሞ እንዲያሰሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ መቀመጫቸውን ካደረጉ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር በበይነ መረብ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያን በውጭ እየደረሰ የነበረውን ጫና በመመከት በኩል ለውጥ ማምጣት ችለው ነበር የተባለ ሲሆን አሁንም በአሜሪካ ኮንግረስና ሴኔት የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ሊቃወሙ ይገባል ተብሏል።

ረቂቁ ከጸደቀ የኢትዮጵያና የአሜሪካን ግንኙነት የሚያበላሽና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ምጣኔ ሀብት የሚጎዳ መሆኑም ተመላክቷል።

በተለይ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በርካታ ሥራዎችን እየሰራች ባለችበት በዚህ ወቅት ረቂቁ አግባብ አይደለም ነው የተባለው፡፡

በሌላ በኩል በሳምንቱ የተለያዩ ምጣኔ ሀብታዊና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች መከናወናቸው ተመላክቷል።

በመስከረም ቸርነት