‘ኤች አር 6600’ እና ‘ኤስ3199’ ረቂቆችን የሚቃወም ሰልፍ ተካሄደ

ሚያዝያ 13/2014 (ዋልታ) ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ.3199’ ረቂቆችን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአሜሪካ ኒው ጀርዚ ግዛት ተካሄደ።

ትናንት በ‘ኤስ.3199’ ረቂቅ ሕግ አርቃቂ ሴናተር ሮበርት ሜኔንዴዝ (ኒው ጀርዚ) ቢሮ ፊት ለፊት በተከናወነው ሰልፍ ላይ “ረቂቅ ሕጎቹ ኢትዮጵያንና ኤርትራን የሚጎዱ ናቸው”፣ ”ማዕቀብ ይገድላል ማዕቀብ ምንም አይቀይርም”፣ ”ኤች አር 6600’ እና ‘ኤስ 3199 ይሰረዙ” እና “ሕጎቹ የኢትዮጵያና አሜሪካን ግንኙነት” የሚጎዱ ናቸው” የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል።

“ሮበርት ሜኔንዴዝ ሽብርተኞችን መደገፍ ያቁሙ”፣ “ሜኔንዴዝ ያረቀቁት ሕግ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያንን የሚጎዳ ነው”፣ “በሴኔት ምርጫው ለሮበርት ሜኔንዴዝ ድምጽ አንሰጥም” እና “የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚጎዳ ተግባር የሚንቀሳቀሱ የአሜሪካ ባለስልጣናትን በምርጫው በድምጽ መቅጣት አለብን” ሲሉ ሰልፈኞቹ መግለጻቸውን ኢዜአ ኒው ዮርክ ኒው ጀርዚ ተስፋ ለኢትዮጵያ ድርጅትን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

በኒው ጀርዚ፣ ኮኔቲከት፣ ፊላደልፊያና ኒው ዮርክ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በሰልፉ ላይ መሳተፋቸው ተገልጿል።

በኒው ጀርዚ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የኒው ዮርክ ኒው ጀርዚ ተስፋ ለኢትዮጵያ ድርጅት፣ ’አሜሪካ ኢትዮጵያንስ ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’ (ኤፓክ) እና የኤርትራ አሜሪካዊያን ብሔራዊ ምክር ቤት በጋራ ያዘጋጁት ነው።

‘ኤች አር 6600’ እና ‘ኤስ.3199’ ረቂቅ ሕጎችን የሚቃወሙ ሰልፎች በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችና ከተሞች እየተካሄዱ መሆኑ ይታወቃል።

በአሜሪካ የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ) ዋና አርቃቂነት፣ በያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን (ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ደጋፊነት የተዘጋጀው ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤች አር 6600 ረቂቅ ሕግ የኮንግረሱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወያይቶበት ለኮንግረሱ መምራቱ የሚታወስ ነው።

የ‘ኤችአር 6600’ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው የኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ.3199’ በአሜሪካ ሴናተር ሮበርት ሜኔንዴዝ (ኒው ጀርዚ) ዋና አርቃቂነት፣ በሴናተር ጀምስ ሪስች (ኢዳሆ)፣ በሴናተር ክሪስ ኩንስ (ዴልዌር) እና በሴናተር ቶም ቲሊስ (ኖርዝ ካሮላይና) ደጋፊነት የተዘጋጀ ሲሆን ሴኔቱ እ.አ.አ በ2022 ሊመለከታቸው በጊዜ ሰሌዳው ከያዛቸው ረቂቅ ሕጎች አንዱ ሆኖ እንዲካተት መወሰኑ ይታወሳል።

በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ረቂቅ ሕጎቹ በሕግ አውጪው አካል ድምጽ ተሰጥቶባቸው እንዳይጸድቁ ለማድረግ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላትን በማናገር፣ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ፊርማ በማሰባሰብና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ በማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው።