ኤፍኤም አዲስ 97.1 በአዲስ አማራጭ ለመምጣት ዝግጅት አጠናቀቀ

ግንቦት 24/2014 (ዋልታ) ኤፍኤም አዲስ 97.1 ለአዲሱ ትውልድ በአዲስ አማራጭ ለመምጣት ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የሬዲዮ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 24 ሰዓት ስርጭት የጀመረው ተቋሙ የተመሰረተበትን 22ኛ ዓመት ሊያከብር መሆኑ ተነግሯል፡፡

የኤፍሬም አዲስ 97.1 ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮናስ ወልደየስ ተቋሙ በኢትዮጵያ የሬዲዮ ታሪክ የራሱን ጉልህ ሚና የተጫወተ ሲሆን አድማጭን ከአድማጭነት ወደ ተሳታፊነት ያሳደገ ነው ብለዋል።

ትውልድን በመቅረጽና በመገንባት ሂደት ውስጥ የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ለውጥ ማምጣት የቻለ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አባይነህ ሙሉጌታ ኢብኮ በተለያዩ ዘርፎች ተቋሙን ተመራጭ እና ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል።

በቴክኖሎጂ፣ በሰው ሀይል እንዲሁም ምቹ የሥራ ቦታን በማመቻቸት ረገድ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኤፍሬም አዲስ 97.1 የተመሰረተው ግንቦት 27 1992 ዓ.ም ነበር።

በመስከረም ቸርነት