ኦሮሚያ ክልል አሸባሪዎችን የማጽዳት እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል አለ

ሚያዝያ 12/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሸኔን የማጽዳት ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስታውቋል፡፡

አሸባሪው ሸኔ ባለፉት አራት ዓመታት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የፈጸመው የጭካኔ ተግባር ቡድኑ ሕዝብን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ዓላማ እንደሌለው ማሳያ መሆኑን ክልሉ ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡

ሰሞኑን እየተወሰደበት ባለው እርምጃ ቀን የጨለመባቸው የቡድኑ አመራሮች የሰው ልጅ ላይ መፈጸም የማይገባ የጭካኔ ተግባር በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እየፈጸሙ መቆየታቸውን እና እየፈጸሙ መሆናቸውን በራሳቸው ላይ ምስክርነት እየሰጡ መሆናቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ መብት የሚረጋገጠው በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ በሚፈጠር የሀሳብ የበላይነት በመሆኑ ቡድኑ ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመለስ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

ቁጥራቸውን ጥቂት የማይባል የኦሮሞ ልጆች እንዳይማሩ ትምህርት ቤት ዘግቶባቸው ቤት እንዲውሉ ማድረጉን ኢብኮ የክልሉን ኮሙዩኒኬሽን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ከሸኔ የበለጠ ጠላት የለውም ያለው መግለጫው ሰሞኑን በቡድኑ ላይ እየተመዘገቡ ያሉ ድሎች የኦሮሞ ሕዝብ በቅርቡ ከቡድኑ እረፍት እንደሚያገኝ ማሳያዎች ናቸው ብሏል፡፡