ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን እንቆማለን – የወላይታ ዞን ነዋሪዎች

የወላይታ ዞን ነዋሪዎች

ሐምሌ 14/2013 (ዋልታ) – ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን እንደሚቆሙ የወላይታ ዞን ነዋሪዎች ባደረጉት የድጋፍ ሰልፍ ገለጹ።

በወላይታ ሶዶ ከተማ የህወሃት ጥቃት የሚያወግዝና ለኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡

ሰልፈኞች ለሀገር አንድነት የሚያስፈልገውን ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

ለሰልፈኞቹ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ የሀገሪቱ ሉዓላዊነት መገለጫ ፕሮጀከት የሆነው የታላቁ የህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የወላይታ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድም ህዝቦች ጋር በመሆን የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከታወጀበት ማግስት ጀምሮ ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙት እስከ ከፍተኛ ባለሀብት፣ ከመንግስት ሰራተኛ እስከ ጡረተኛ፣ ከነጋዴ እስከ አርሶአደር፣ ከአስተማሪ እስከ ተማሪ ቦንድ በመግዛትና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ግድቡ ለዚህ ደረጃ እንዲደርስ የበኩሉን ድርሻ መጫወቱን ጠቁመዋል።

የዛሬው የሕዳሴ ግድብ ስኬት እኛ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከተነሳን ከባድ የሚባሉ ተግዳሮቶችን ማሸነፍ እንደምንችል ትልቅ ትምህርት ያገኘንበት በመሆኑ ሁሉም የዞኑ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቱ የገጠማትን ተግዳሮት ለመሻገር በጋራ እንዲነሳ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ሽብርተኛው የህወሀት ቡድን ስግብግብ ፍላጎቱን ለማሟላት በለጋ ዕድሜ የሚገኙ ህጻናትን ጭምር ወደ ጦር ሜዳ በመሰማራት የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ በመሆኑ ድርጊቱን የዓለም ማህብረሰብ በጽኑ ሊያወግዘው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ዘረኛና ከፋፋይ ሽብርተኛው የህወሀት ቡድን እንዲደመሰስ መከላከያ ሰራዊት እያደረገ ላለው ተጋድሎ ስኬታማነት እንደ ሌሎቹ የሀገሪቱ ህዝቦች ሁሉ የወላይታ ዞን አስተዳደርና ህዝብ እንደ ቀደምት ጊዜያት ሁሉ ለሰራዊታችን የሚያደርገውን የቁሳቁስ፣ የገንዘብ፣ የሞራልና ሌሎች ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር እንድሪያስ አረጋግጠዋል።

በማያያዝም 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ የገለጸው ሰላም ወዳዱ ህዝብ እንደ ወትሮው ሁሉ ሰላም በማስከበር የተጀመሩ የልማት ስራዎች ፍጥነትና ቀጣይነት እንዲረጋገጥ የድርሻቸውን በተነሳሽነት እንድወጣ ማሳሰባቸውን ከዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።