ከህግ ውጪ በሰሩ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ሚያዝያ 13/2014 (ዋልታ) ባለፉት 9 ወራት በድህረ ፈቃድ ክትትል ከተደረገባቸው 912 ድርጅቶች ውስጥ 96 ድርጅቶች በህግ አግባብ እየሰሩ ባለመሆኑ አስተዳዳረዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የገበያና ፋብሪካ ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር ተከተል ጌቶ እንደገለጹት ከድርጅቶች ውስጥ በ71 የንግድ ድርጅቶች ላይ የንግድ ፈቃድ እገዳና እሽጋ እንዲሁም በ25ቱ ድርጅቶች ላይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የመስጠት እርምጃ ተወስዷል፡፡

በተጨማሪም በ344 ድርጅቶች ላይ በፋብሪካዎች እና ገበያ ቦታዎች በተደረገ የክትትል ሥራ ከ30 የምርት አይነቶች ላይ 195 ወካይ ናሙናዎች መወሰዳቸውን ገልጸው 86 ድርጅቶች የተቀመጠውን የጥራት ደረጃ ያሟሉ መሆናቸው እንደተረጋገጠና የ48 ድርጅቶች ምርት ጥራት ከደረጃ በታች መሆኑ በመረጋገጡ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡

ከ48ቱ ድርጅቶች ውስጥ 31 አምራች ፋብሪካዎች ከማምረት ሂደታቸው እንዲታደጉ ተደርጎ የማስተካከያ ሥራዎች ከሰሩ በኋላ በድጋሚ ምርቶቻቸው በላቦራቶሪ ፍተሻ ተረጋግጦ ወደ ሥራ እንዲመለሱ መደረጉን፣ ለ5 ፋብሪካዎች የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም በ12 አስመጭዎች ላይ የንግድ ፈቃድ እገዳ እርምጃ መወሰዱንም አመልክተዋል፡፡

ሁሉም አስመጪዎችና እና አምራቾች በኅብረተሰብ ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ምርቶችን ከማምረት እና ከማሰራጨት በመቆጠብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ በማሳሰብ በቀጣይ በህገ ወጦች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW