ከምግብ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ 114 ነጥብ 29 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ

ጥቅምት 11/2015 (ዋልታ) በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪዎች በ2014 በጀት ዓመት 114 ነጥብ 29 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኤክስፖርትና ተኪ ምርት ለማሳደግ በተዘጋጀው የንቅናቄ መድረክ እንደተገለጸውም በ2014 ከዘርፉ 110 ነጥብ 97 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ በአፈጻጸም 114 ነጥብ 29 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን ይህም በ 2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ከተገኘው የ 91 ነጥብ 80 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነጻጸር የ124 በመቶ ጭማሬ አሳይቷል፡፡
የብርዕና አገዳ ሰብሎች እና የቅባት እህሎች ፕሮሰሲንግ ምርቶች ለገቢ ግኝቱ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው በዘርፉ የቀረበው ሪፖርት ያመላክታል፡፡
የዘርፉን 2014 በጀት ዓመት አፈፈጻጸምን ተከትሎም በወጪ እና ተኪ ምርቶች ለገቢ ግኝቱ ከፍተኛ አስተዋዕጾ ላበረከቱ ሴት ላኪዎች፣ አጋር አካላትና ድርጅቶች እንዲሁም የመንግስት ባለድርሻ አካላት የዕውቅናና ምስጋና ስነ-ሰርዓት መከናወኑም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
የንዑስ ዘርፉን በተመረጡ ስትራቴጂክ ተኪ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ፣የዘርፉ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ውጤታማ ስራዎች ለመስራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡