ከረቂቅ አዋጁ ይዘት ውጪ በተለያዩ  ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች ሀሰተኛ ናቸው – የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር

ጥር 15/2014 (ዋልታ) የክልል መለያን የያዙ ሰሌዳዎችን የሚያስቀር ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ተመራ በሚል በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተሠራጨ ያለው መረጃ የተሳሳተ መሆን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቋል፡፡

ከረቂቅ አዋጁ ይዘት ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎችን  በተመለከተ ሚኒስቴሩ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በመግለጫውም በቅርቡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመንገድ ትራንስፖርት ረቂቅ አዋጅ ላይ አስፈላጊውን ግብዓቶች በማካተት እንዲፀድቅ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መምራቱን አስታውሷል፡፡

ሆኖም ግን ከረቂቅ አዋጁ ይዘት ውጭ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የክልል መለያ ከተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ መመራቱን የሚገልጽ ዜና እየተዘገበ ስለመሆኑ አረጋግጠናል ብሏል ሚኒስቴሩ ፡፡

“በመጀመሪያ መረጃዉ የተሳሳተና ከረቂቅ አዋጁ ይዘት ውጭ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን” ሲልም ገልጿል፡፡

በመቀጠልም “በቀድሞ አዋጁ የነበረዉ የተወሰኑ ክልሎችን ታርጋ ዝርዝር የያዘ አባሪ በዚህ ረቂቅ አዋጅ የቀረው መንግሥት ተጨማሪ ክልሎች ሲወጡ በየጊዜዉ በአዋጁን ማሻሻል ሳያስፈልገዉ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲችል ታስቦ መሆኑ ታውቆ የክልል መለያ ሰሌዳን ከተሸከርካሪዎች ላይ የማንሳት የረቂቅ አዋጁ ሀሳብና ይዘት አካል እንዳልሆነ ሊታወቅ  ይገባል” ሲልም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የመንገድ ትራንስፖርትን አስመልክቶ የፌዴራሉንና የክልል አስፈጻሚ አካላት የተሰጣቸውን ሥልጣንና ተግባር በማያሻማ ሁኔታ የሚያስቀምጥ ከመሆኑም በላይ ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ የበለጠ ለማጎልበት ዘርፉ አስተማማኝ፣ የተቀናጀ፣ ዘመናዊና ደኅንነቱ የተረጋገጠ ሆኖ እንዲራመድ የሚያስችል እንደሆነና በቅርቡም ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርቦ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎና አስፈላጊዉ ማሻሻያ ተደርጎበት እንደሚጸድቅ  ከሚኒስቴሩ ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል፡፡