ከቀረጥ ነፃ የቆዳ እና ቆዳ ውጤቶች መሸጫ ሱቅ በይፋ ተከፈተ

ነሐሴ 27/2014 (ዋልታ) የኢንዱስተሪ ሚኒስቴር ከአጋር አካላቱ ጋር በመሆን በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ከቀረጥ ነፃ የቆዳ እና ቆዳ ውጤቶች መሸጫ ሱቅ በይፋ አስመርቋል።

የመሸጫ ሱቁ መከፈት ዋናኛ ዓላማም የኢትዮጵያን ምርቶች ማስተዋወቅ እና የዘርፉን ወጪ ንግድ ማሳደግ እንደሆነ ተገልጿል።

የኢንዱትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው፣ በዘርፉ ሁለንተናዊ እድገት ለማምጣት ከአጋር አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የወጪ ንግድ ገቢን፣ የማምረት አቅም አጠቃቃምን በማሳደግ እና የገጽታ ግንባታ ሥራ በመሥራት በኩል እንደ ሀገር ለተጀመረው ኢትዮጵያ ታምርት አገራዊ ንቅናቄ መሳካት የዚህ ፕሮጀክት እውን መሆን አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል።

ምንም እንኳን ፕሮጀክቱ ጅምር ቢሆንም ባለፉት ሁለት ወራት 200 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከሽያጭ ማዕከሉ መገኘቱን እና አበረታች ውጤቶች እየታየ መሆኑን ገልጻዋል።

በ2014 በጀት ከቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ወጪ ንግድ 40 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የጃፓን ኮርፖሬሽን (JICA) የኤክስፖርት ማስተዋወቅ ፐሮጀክት ዋና አማካሪ ኖሪክ ናጋይ፣ ድርጅታቸው የኢትዮጵያን ቆዳ እና ቆዳ ውጤቶች በተለይም የሃይላንድ ቆዳ በሚል የሚታወቀውን ብራንድ ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረረገ ነው ማለታቸውን የሚኒስትሩ መረጃ ያመለክታል።