ከተማ አስተዳደሩ ከ600 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የማዕድ ማጋራት መርኃግብር አካሄደ

የማዕድ ማጋራት መርኃግብር

ሚያዝያ 13/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ600 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የማዕድ ማጋራት መርኃግብር ከ195 ሺሕ በላይ የከተማው አቅመ ደካሞች አከናውኗል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መርኃግብሩ ዓለም ላይ ብሎም በሀገሪቱ የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት ለማቃለል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘላቂነት ችግሩ እስኪፈታ ድረስ ችግሩን ለማቃለል መደጋገፍ ተገቢነት እንዳለውም ከንቲባዋ አንስተዋል።

በማዕድ ማጋራቱ ዝቅተኛ ወይም ምንም ገቢ የሌላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የመንግሥት ሰራተኞችና የፀጥታ ኃይሎችን ያካተተ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

አሁን ያለው የዋጋ ንረት የሚያስከትለውን የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቋቋም ከተማ አስተዳደሩ በተለይ በበዓል ወቅት ዜጎች በመተሳሰብና ያለውን የማካፈል ባህል እንዲጠናከር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

ከሚያዝያ አንድ ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የማዕድ ማጋራት የዛሬውን ቀን ሳይጨምር 43 ሺሕ 386 የማዕድ ማጋራት ማከናወን መቻሉ ታዉቋል፡፡

የዛሬውን ጨምሮ የማዕድ ማጋራቱ በጥቅሉ 240 ሺሕ መድረሱን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

የማዕድ ማጋራት መርኃግብር

በአጠቃላይ ማዕድ ማጋራት ሥነ ሥርዓቱ 600 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ሆኖ ከዚህ ውስጥ 500 ሚሊዮን የሚሆነው ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ አስተዳደራዊ ወጪዎችን በመቀነስ የተመደበ ሲሆን ቀሪው 100 ሚሊዮን ደግሞ የከተማውን ባለሀብቶች (አዋሽ ባንክ፤ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፤ ሆራ ትሬዲንግ ኤም፣ MWS ትሬዲንግ) በማስተባበር የተሰበሰበ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡

በዙፋን አምባቸው

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!